
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሰጡ ማለደ በሹፍርና ሥራ ይተዳደራሉ። አሁን ላይም ሪህ መታመማቸውን አነሱልን። መንስኤውም ደግሞ ሥጋ አብዝቶ በመመገብ ምክንያት የኮሌስትሮል መጠን መብዛት መኾኑ በሐኪም ተነግሯቸዋል።
በሽታው አንዴ ከያዘ በኋላ ማስታገስ እንጂ መዳን እንደማይችል የተነገራቸው አቶ ሰጡ ማለደ ሥጋን እና ሥጋን የሚተኩ ምግቦችን ከመመገብ ተቆጥበው የአትክልት ምግቦችን እንዲመገቡ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲያደርጉ በባለሙያ ተመክረዋል።
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የሥርዓተ ምግብ መምህር እና ተመራማሪ መልካሙ አደራጀው በበዓላት ወቅት አመጋገብ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ይላሉ።
መምህሩ ሰዎች በዓላትን ተከትለው የሥጋ ውጤቶችን፣ ቅባት እና ቅመማቅመም የበዛባቸው ምግቦችን በአግባቡ ካልተመገቡ የጤና እክል ሊገጥማቸው እንደሚችል ገልጸዋል።
አብዛኞቹ በዓላት የሚከበሩት ከጾም ቀጥሎ በመኾኑ የሰውነት የምግብ ሥርዓት ለምዷቸው ከቆዩት ምግቦች የተለየ ይኾኑበታል፤ ይህም የአመጋገብ ሥርዓትን ስለሚያዛቡ ለጤና መታወክ ይዳርጋል ነው ያሉት።
በጾም ወቅት የጾም ምግቦችን በአነስተኛ መጠን መውሰድ የለመደ የአንድ ሰው ጨጓራ እና አንጀት በበዓል የፍስክ ምግቦችን ለመቀበል እንደሚከብደው ነው የገለጹት።
ሰውነት ለጾም ምግቦች ሲያመነጫቸው የነበሩት ኢንዛይሞች እና ኬሚካሎች የፍስክ ምግብ ሲመገቡ ስለሚቀየር ሰውነት የሚሰጠው ምላሽ ጤናማ እንደማይኾን ተናግረዋል።
በበዓል ሰሞን ጮማ እና ቅባታማ ምግቦች ሲወሰድ የምግብ አለመፈጨት እና ምቾት ማጣትን ያስከትላልም ብለዋል።
ደም ግፊት እና ስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎችም ሥጋ እና ቅባታማ ምግቦችን ሲመገቡ የስኳር እና የደም ግፊት ልኬታቸው ከቁጥጥር ውጭ ሊኾን ይችላል ነው ያሉት።
ቅባታማ ምግቦችን፣ የጨው መጠንን፣ ስኳርና ሌሎች ማጣፈጫዎች የበዛባቸውን ምግብ እና መጠጦች በብዛት ባለመውሰድ በበዓላት ወቅት ጤናን መጠበቅ እንደሚገባም አብራርተዋል።
ከሥጋ ጋር አትክልቶችን መመገብ ሰውነት በጾሙ የለመዳቸው ምግቦች ስለሚቀርቡለት ለጤና ተስማሚ እንደሚኾን ገልጸዋል፡፡
በበዓላት ከአልኮል እና ጣፋጭነት ካላቸው መጠጦችም መታቀብ አለያም መጠናቸውን መወሰን አስፈላጊ እንደኾነ አንስተዋል፡፡ ለስላሳ መጠጦችም ስኳር ስለሚበዛባቸው የጤና ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።
ከሥጋ እና ቅባታማ ምግቦች ላይ አልኮል ሲጨመርበት ለጨጓራ የማይስማማ መኾኑንም አንስተዋል። በበዓል ወቅት መገባበዝ ስለሚበዛ ያንን ታሳቢ ያደረገ አመጋገብ ሊኖር እንደሚገባ ተመራማሪው መክረዋል።
ብዙ ጊዜ አልኮል መጠጣት ክብደት ይጨምራል ያሉት መምህር መልካሙ በዚህም የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የጉበት እና የልብ በሽታ እንደሚያስከትል አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
