“ሰማይ የተገለጠብሽ፤ ምድር የተዋበችብሽ”

25
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንቺ ሰማይ የተገለጠችብሽ፣ ምድርም የተዋበችብሽ፤ መንፈስ ቅዱስ የረበበብሽ፣ ቅዱሳኑ በሰርክ የሚመላለሱብሽ፤ ደጋጎቹ የጠለሉብሽ፤ የአምላክ ጥበብ የተገለጠብሽ፤ ሰማይ እና ምድር በአንድነት የሚታዩብሽ፤ ሰው እና መላዕክት የተባበሩብሽ ቅድስት ምድር ሕዝብ ሁሉ ይናፍቅሻል።
አንቺ የዓለም ጥበብ ሁሉ የማይተካከልሽ፣ ከምድር ጥበብ ሁሉ የላቅሽ፣ እጹብ እጹብ የተሰኘሽ፤ ለምድር ጠቢባን ከጥበባቸው በላይ የኾንሽ ድንቅ ምድር ኾይ ትውልድ ሁሉ ያደንቅሻል።
አንቺ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን የመሰለሽ፤ ዳግማዊት ኢየሩሳሌም የተባልሽ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት በዓለት ላይ የተቀረጹብሽ፤ ቅዱስ መጽሐፍ በዓለት ላይ ተጽፎ የሚነበብሽ፤ ዓለት እንደ አሽከር የታዘዘብሽ፤ እንደ ግራምጣ የተሰነጠቀብሽ፣ ታሪክ እና ሃይማኖት የረቀቀብሽ፤ ክብርና ከፍታ የተገለጠብሽ ቅድስት ምድር ኾይ እየታየሽ ትናፈቂያለሽ። እየኖሩብሽ ታጓጊያለሽ፤ ጀንበር ጠልቃ በዘለቀች ቁጥር ሰርክ አዲስ ትኾኛለሽ።
አንቺን እንኳን በዓመት አንድ ጊዜ ሄደው የሚያዩሽ፤ ባሕር አቋርጠው፣ የብስ ሰንጥቀው የሚጎበኙሽ ይቅርና፤ በሠርክ እጅ የሚነሱብሽ፤ ኪዳን የሚያደርሱብሽ፤ ቅዳሴ የሚቀድሱብሽ ሊቃውንቱ እንኳን ሁልጊዜም አዲስ ትኾኝባቸዋለሽ፤ በሠርክ እንደ አዲስ እያዩ ይደነቁብሻል፤ በሠርክ አንቺን የሠራውን ቅዱስ አገልጋይ፣ እንዲሠራ ያደረገውን ቅዱስ አምላክ ያመሰግኑብሻል ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ።
በዚያች ሥፍራ በሰማይ ያሉ ምስጢራት ተገልጠዋል፤ በዚያች ሥፍራ ረቂቃኑ በጥበብ ታይተዋል፤ በልቡና ውስጥ ያሉት በረረቀ ጥበብ ተዳስሰዋል። ደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ኢትዮጵያውያን ከዓለም ልቀው የሚታዩባት፤ የዓለሙን ትኩረት የሚስቡባት፤ ከዓለም ጥበብ ሁሉ በልጠው የተቀመጡባት፣ የሌላውን ዓለምም ንቀው የራሳቸውን ጥበብ ያስቀመጡባት ቅድስት ስፍራ ናት።
ኢትዮጵያውያን ነገሥታት መስቀል ይዘው ይባርካሉ፣ በትረ መንግሥት ጨብጠው ሀገር ይመራሉ፤ በአንድ ጎን የቤተ ክህነቱን፣ በሌላ ጎን የቤተ መንግሥቱን ሳያቀላቅሉ በሚዛን ያስተዳድራሉ። የእውነት ይኖራሉ፤ ለእውነት ይኖራሉ፤ በእውነት ይመራሉ።
በምድር ንጉሥ በሰማይ ቅዱስ ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ቅድስናን ከንግሥና ጋር አሥተባብረው ከኖሩ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት መካከል ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ አንደኛው ናቸው።
እኒህ ቅድስናን ከንግሥና ጋር አሥተባብረው የኖሩት ቅዱስ በድንኳን እየኖሩ የእግዚአብሔርን ቤት በዓለት ላይ አንጸዋል፤ ምድራዊ ቤተ መንግሥትን ሳይኾን በምድር ኾነው ሰማያዊ መንግሥታቸውን ገንብተዋል።
እንደ ንጉሥ ተድላን አልፈለጉም፤ ጠግቦ መብላትን፤ አብዝቶ መጠጣትን አልወደዱም ይልቅስ ስጋቸውን እያዳከሙ ነፍሳቸውን አበረቱ እንጂ። አለት ጠርበው ኢትዮጵያውያን ለዘላለም የሚመኩባቸውን፤ ስማቸው የሚነሳባቸውን፤ አምላክ በሠርክ የሚመሰገንባቸውን አብያተ ክርስቲያናት አነጹ።
በቅድስና ዓለትን ያዘዙት፤ በዓለት ላይም ረቂቁን ሥራ የሠሩት ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ስማቸው በማይጠፋ ብራና ላይ ተጽፎ ይኖራል። እርሳቸው የሠሯት ቅዱሷ ከተማም ለዘላለም ትናፈቃለች፤ ይህችን ቅድስት ሥፍራ የሠሩ እጆች የተባረኩ ይሁኑ እየተባሉ ይመሰገናሉ።
ጨርሰው የጀመሩት፤ ቤተ መቅደስ ከጣሪያ ወደ መሠረት የሠሩት፣ ምስጢራዊት ቅድስት ከተማ ያነጹት ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ የጥበባቸው ነገር እጹብ እየተባለ ይወራል። ግሩም ድንቅ እየተባለ ለትውልድ ሁሉ ይነገራል።
ዲያቆን ፈንታ ታደሰ የዐራቱ ቅዱሳን ነገሥት እና የአካባቢው ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ንጉሥ ወቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ነኝ እና ጮማ ልቁረጥ፣ እራሴን ከፍ ላድርግ ሳይሉ አምላካቸው የፈቀደላቸውን ነገር ለማድረግ ሁሌም ያስቡ ነበር ብለው ጽፈዋል። በዚህ ትህትናቸው የረቀቀችውን ሥራ አኑረዋል።
በገድለ ቅዱስ ላሊበላ እንዲህ ተጽፏል። ሕንጻዎቹ ግሩም እና አስደናቂ ናቸው። ተወዳዳሪም የላቸውም። በዓለምም ተመሳሳይ አልተገኘላቸውም። የእነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ሥራ መናገር በምን አንደበት እንችላለን? የውስጣቸውንስ እንተውና የቅጽራቸውን ሥራ እንኳ መናገር አንችልም፤ ያየም በማየት አይጠግብም። ልቡ አርፎ ከማድነቅ ቸል አይልም። ታሪኩን ይቆጥር ዘንድ ለሰው የማይቻለው በላሊበላ ድንቅ የኮነ ታሪክ ተሠርቷልና።
በላሊበላ እጅ የተሠሩትን አብያተ ክረስቲያናት ሕንጻ ሥራ ያይ ዘንድ የሚወድ ሰው ቢኖር ይምጣ ባይኖቹም ይይ እንደ ሙሴ ድንኳን የላሊበላ አዳራሾች የሚያረጁ አይደሉም ወይም እንደ ሶሎሞን አዳራሽ ጠላቶች የሚያፈርሱት አይደለምና።
የላሊበላ አዳራሾችስ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት በምድር ላይ እስክትታይ ድረስ አይነዋወጥም። አይጠፋምም። ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደሰም አለምልመው በሦስት ድንጋዮች የቅድስት ድንግልን የቤተ መቅደስ ሕንጻ ጨረሱ።
ላሊበላም እንደዚሁ ጸጋ እግዚአብሔር እየረዳው ካንድ አለት ድንጋይ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራ። ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ደግሞ በአንድ ጭንጫ ላይ አብያተ ክርስቲያናት ሠሩ። ሥራቸው ግን የጣራው ዕንጨት በገመድ የተታታ፣ ግድግዳውም የእንጨት ነው፤ ምርጊቱም ጭቃ፣ ምስሶዎቹ ዕንጨቶች ናቸው፡፡
ላሊበላ ግን ካንድ አለት ድንጋይ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ሢሠራ ለግድግዳቸው ዕንጨት ለመሠረታቸውም ጭቃ፣ ለጣራቸውም ባጥ ዕንጨት እና የገመድ ትት፣ ለክዳናቸውም የሰንበሌጥ ሣር የላቸውም። የአሠራራቸውም ሁኔታ ብዙ ስለኾነ ሥራቸውን ሁሉ በየመልኩ በየዓይነቱ ዘርዝረን ልንናገር አንችልም ተብሎ ተጽፏል።
ኢትዮጵያዊ ኾኖ ካንዲት ድንጋይ የተሠሩትን የነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ዜና ሰምቶ ቅድስት ወደኾነችው ወደ ሮሐ ያልደረሰ እና ይህንን ያላየ የጌታችን እና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ፊት ያይ ዘንድ የማይወድ ሰው ይመስላል ይላል።
እነኾ ያቺ በሠርክ ሰው የማይጠፋባት፣ ሰማይ የተገለጠችባት፣ ምድርም የተዋበችባት ከተማ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በደረሰ ጊዜ በእልፍ አዕላፋት ምዕምናን፣ በዲያቆናት፣ በቀሳውስት፣ በመነኮሳት፣ በጳጳሳት ትከበባለች። ምድራዊ፣ ሰማያዊ የመሰለ ዝማሬ ይቀርብባታል። ጌታ በተወለደ ጊዜ በቤተልሔም የተፈጸመው ይፈጸምባታል።
እነኾ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ደርሷል፤ ሮሐ ነጫጭ ለብሰው የሰላም እርግብ በመሰሉ ምዕመናን ተመልታለች፤ በደጋጎቹ ተከባለች።
ኢትዮጵያ በታሪኳም፤ በባሕሏም ልዩ ናት። ድንቅ ምስጢር አላት። የቅዱሳን ሀገር ናት እና ክብሯ እና ሞገሷ አምላኳ ነው፡፡ በዜማ የምትቀደስ በቅኔ የምትወደስ ሕያዊት ሀገር ናት፡፡
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።
Next articleበበዓላት ወቅት አመጋገባችን እንዴት ይሁን?