በክልሉ ለግብርና ሜካናይዜሽን ትኩረት ተሰጥቷል።

13
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ሜካናይዜሽን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የአመራረት ዘዴ በመኾኑ ግብርናውን ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና አለው።
መሬትን ከማረስ ጀምሮ ምርትን እስከ መሰብሰብ ድረስ የሚባክነውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ በመቀነስ ምርትን በጥራት ለማምረት ያስችላል።
አርሶ አደር ይርጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን
በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ጃቢ ገነት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በትራክተር እና በኮምባይነር በመታገዝ የእርሻ ሥራቸውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጅን በመጠቀማቸው ምርታቸውን እያሻሻሉ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
በሰሜን ሸዋ ዞን የሞረት እና ጅሩ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አደፍርስ አርጋው በክላስተር ዘዴ፣ በኮምባይነር እና ትራክተር በመጠቀም የተሻለ ምርት እንደሚያመርቱ ገልጸዋል። ወጭን እና ጊዜን በመቀነስ ምርትን በጥራት ለማምረት እንደሚያስችልም በተግባር አይተንበታል ብለዋል።
የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌትነት ሰዋለም በወረዳው 4 ትራክተሮችን በመጠቀም ሜካናይዜሽን እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል። ከራሳቸው እና ከሌሎች ወረዳዎችም በማምጣት 15 ኮምባይነሮችን በመጠቀም 23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር የለማ ስንዴን መሠብሠብ መቻላቸውንም ተናግረዋል።
የሞረት እና ጅሩ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ዓለማየሁ ደግሞ በወረዳው በ18 ትራክተሮች፣ በ5 ኮምባይነሮች እና በ76 ትናንሽ የመውቂያ ማሽኖችን እየተጠቀሙ እንደኾነ ተናግረዋል።
ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ በኾነ መሬት የለማን የስንዴ ምርት ሙሉ በሙሉ ኮምባይነር በመጠቀም እየተሰበሰበ ነው ብለዋል። በቀጣይም የኮምባይነሮችን ቁጥር ወደ 10 ፣ ትራክተሮችን ደግሞ ወደ 23 ለማሳደግ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) በክልሉ የሜካናይዜሽን አሠራር መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ነው ብለዋል።
በዘንድሮው የምርት ዘመን ከታረሰው 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በትራክትር የታረሰ ነው ብለዋል። ለዚህም 1ሺህ 795 ትራክተሮች ጥቅም ላይ ውለዋል ነው ያሉት።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ሰብል 76 ኮምባይነሮችን በመጠቀም መሠብሰቡን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 119 ሁለገብ የመውቂያ እና 13 የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችንም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ መኾኑን አመላክተዋል።
በሚቀጥለው የምርት ዘመን የሜካናይዜሽን አሠራርን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleአዋሽ ባንክ ከ200 በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።
Next article“ወደ አዕምሮአችን እንመለስ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ