
ደሴ: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሕገወጥ እና ኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል ግብረ ኀይል የክልል እና የዞን የኑሮ ማረጋጋት ሥራ ላይ የጋራ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በግብረ ኀይሉ የተካተቱ ተቋማት የግል እና የጋራ ተልዕኳቸውን ተገንዝበው የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ሕገ ወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን በማስወገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ ነው።
የኮምቦልቻ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ በባለፉት ስድስት ወራት 623 ሕገ ወጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች መያዛቸውን እና በመምሪያው እርምጃ መወሰዱን እና ለሕግ መቅረባቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም መሰል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ እና የሕገ ወጥ እና ኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል ግብረ ኀይል ኮሚቴ አባል አብዱልከሪም መንግሥቱ ፈቃድ የሌላቸው መድኃኒቶች በኮንትሮባንድ ጥቅም ላይ እየዋሉ የማኅብረሰቡን ጤና አደጋ ላይ እየጣሉ መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ያለ ፈቃድ 1 ሺህ 60 የሚኾኑ የመድኃኒት መደብሮች የከፈቱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ግብረ ኀይሉ መለየቱን ያነሱት አቶ አብዱልከሪም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምግብ እና መጠጦች ከሦስት ቶን በላይ መወገዱንም ጠቁመዋል።
ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ማኅበረሰቡ ተባባሪ እንዲኾንም አቶ አብዱልከሪም ጠይቀዋል።
ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በክልል ብሎም በሀገር ኢኮኖሚ እንዲኹም በዜጎች የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በቅንጅት ለማስወገድ እየተሠራ መኾኑን ያመላከቱት ደግሞ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) ናቸው።
ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የቅንጅት ሥራን እንደሚጠይቅ እና በዚህ ዘርፍ የተሰማሩትን የመለየት ሥራ ማከናወን እንደሚገባም አመላክተዋል።
ሕገ ወጥ ተግባራት ሲሠሩ ተቋማት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ በክፍተት የሚታይ መኾኑንም አንስተዋል ቢሮ ኀላፊው።
ዘጋቢ:-ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
