በአማራ ክልል በእንስሳት ሃብት ልማት ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ ነው።

21
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ነጋ

ይስማው ዘርፉን ለማልማት እየተሠሩ ባሉት ተግባራት ዙሪያ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ምክትል ኀላፊው እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ልዩ ትኩረት ከተሰጡት ዘርፎች መካከል አንዱ ነው።ቢሮው ከክልሉ የ25 ዓመታት አሻጋሪ እቅድ እና የአምስት ዓመታት ስትራቴጅክ እቅድ ጋር በማስተሳሰር ዘርፉን ሊለውጥ የሚችል እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል።

በዘመናዊ መንገድ በመምራትም በወተት፣ በሥጋ፣ በእንቁላል፣ በዓሣ እና በማር ምርቶች ላይ ስትራቴጅ ተነድፎ እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል። የወተት ምርትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻል ላይ በመሥራት በወተት ምርት ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።ለእንስሳት ሀብት ልማት ምርታማነት ዋነኛ መሠረቱ መኖ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው በክልሉ ከ42 በላይ የመኖ ማቀነባበሪያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። እነዚህን ማቀነባበሪያዎች በጥራት እንዲያመርቱ የክትትል እና ድጋፍ ሥራ እንደሚሠራ አንስተዋል። በቀጣይም ተጨማሪ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንደሚገቡ አመላክተዋል።የተሻሻለ የመኖ ዘር በችግኝ ጣቢያዎች በማሥፋፋት፣ የገፈራ እና የምጥን መኖ ዝግጅትን በተጠናከረ መንገድ እንዲሠራበት ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአንድ ቀን ጫጩት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍም የክልሉ መንግሥት ትኩረት በመሥጠት የጫጩት መፈልፈያ ማዕከላትን እየገነባ መኾኑን ተናግረዋል። 100 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የኮምቦልቻን የዶሮ ብዜት ማዕከልን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ሌሎች ተጨማሪ የጫጩት መፈልፈያ ፋብሪካዎችንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለማሥገንባት ዝግጅት እየተደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። በዚህም የአንድ ቀን ጫጩት እጥረት በክልሉ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፍ አመላክተዋል።
ግብዓቶችን በማሟላት እና ቴክኖሎጅን በመጠቀም በክልሉ በእንስሳት ሀብት ልማት ውጤት ለማምጣት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleለበዓል በቂ የእንቁላል እና ዶሮ አቅርቦት አለ።
Next articleሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ነው።