
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የበዓል ወቅት ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን ለመሸመት ጥረት የሚያደርግበት ነው።
በተለይ እንዲህ እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲኾን ደግሞ አማኙ ጾሞ ለመግደፍ ኪሱ በፈቀደ ልክ የጾም መፍቻ ለማሟላት ጥረት የሚያደርግበት ጊዜም ነው።
በዚህ ሁኔታ ታዲያ ገበያ ላይ የሚኖረው አቅርቦት በስፋት እና በጥራት ሊኾን እንደሚገባ ይጠበቃል።
አቅርቦቱም ገዥዎች በሚፈልጉት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲኾን መፈለጋቸው አይቀሬ ነው።
ለመኾኑ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ለማክበር ገበያው ምን ያክል ጥጋብ እንደኾነ አሚኾ የባሕርዳር ከተማን ገበያ ለመቃኘት ሞክሯል።
በተለይም በዓሉን የሚያደምቀው የእንቁላል እና ዶሮ ምርት አቅርቦት እና ጥራትን በልዩ ሁኔታ ለመቃኘት ሞክሯል።
ወጣት ሙሉ ብርሌው በባሕር ዳር ከተማ በዶሮ እርባታ ላይ ተሠማርቶ እየሠራ ነው። ወጣቱ ለበዓል ገበያ በርከት ያለ እንቁላል እና ዶሮ ለገበያው ማቀረቡንም አንስቷል።
ወጣቱ በከተማው በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማሩ በርካቶች በመኾናቸው የአቅርቦት ችግር እንደማይኖር ነው የተናገረው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ውለታው አዳነ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶችን በበቂ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ከአምራቾች እና ከኢንተርፕራይዞች ጋር በመመካከር በቂ ዝግጅት ተደርጎ ለሸማቾች እየቀረበ መኾኑን ጠቅሰዋል።
መምሪያ ኅላፊው እንደገለጹት በከተማው ላይ አጠቃላይ 328ሺህ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች ያሉ ሲኾን በዓመት 32ሚሊዮን በላይ እንቁላል ይመረታል ነው ያሉት።
እስካሁን በስድስት ወር ውስጥ 23ሚሊዮን እንቁላል እንደተመረተም ነው ያስረዱት።
በከተማ ደረጃ 32 የምርት መሽጫ ሱቆች፣ 125 ኢንተርፕራይዞች፣ 169 አሳዳጊዎች እና 3ሺህ 750 በላይ የተናጠል አርቢዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
እነዚህን ሁሉ በመጠቀምም በስድስት ክፍለ ከተሞች በሁሉም ሱቆች ላይ ለበዓል እንቁላል እንዲቀርብ ተደርጓልም ነው ያሉት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በተመለከተ ባዛሮች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።
በየባዛሮቹም በቂ ምርት በመያዝ ለበዓሉ አስፈላጊ የኾኑ ግብዓቶች ለግብይት መቅረባቸውን እና ተጠቃሚዎችም የአቅርቦት ችግር አለመኖሩን ተረድተው ተረጋግተው እንዲገዙ መክረዋል።
የእንቁላል ዋጋ ከ14 ብር እስከ 16 ብር እንዲሽጥ ከአምራቾች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም አንስተዋል።
ኅብረተሰቡም ለበዓል የተፈጠሩ ዕድሎችን በመጠቀም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት መገበያየት ይችላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
