
ደሴ፡ ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማዋን የትራንስፓርት እጥረት ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት የደሴ ከተማ አሥተዳድር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው አምስት አውቶቡሶች ተገዝተዋል ነው ያሉት።
በከተማ አሥተዳደሩ ምቹ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መኾኑን ያመላከቱት ከንቲባው የተቀላጠፈና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ከወዲኹ ሥራዎችን ጀምረናል ብለዋል።
አውቶቡሶቹ በተለይ ዝቅተኛ ነዋሪ የኀብረተሰብ ክፍሎችን፤ አካል ጉዳተኞችን እና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
የደሴ ከተማ ትራንስፓርትና ሎጅስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወንድወሰን አባተ የተገዙት አውቶቡሶች በኤሌክትሪክ የሚሠሩ በመኾናቸው በተለይም የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሚገጥም ጊዜ በትራንስፖርት ችግር የሚንገላታውን ማኀበረሰብ ችግር የሚቀርፉ ናቸው ብለዋል።
በቅርቡ ለማኀበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የተናገሩት አቶ ወንድወሰን ነዋሪዎች በእኔነት ስሜት እና በጥንቃቄ በአገልግሎቱ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
በአንድ ጊዜ ቻርጅ ከ350 ኪ.ሜ በላይ የመጓዝ
አቅም ያላቸው መኪኖቹ ለአቅመ ደካሞች መውጫና መውረጃ እንዲሁም ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ እንደተገጠመላቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ጀማል ይማም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
