
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ እየተሠሩ ከሚገኙ ሥራዎች ውስጥ የእንግዶችን ጤንነት መጠበቅ አንዱ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ለመታደም ወደ ላሊበላ የሚመጡ እንግዶች ጤንነት ተጠብቆ ወደ መጡበት እንዲመለሱ በእንግዶች ማረፊያ አካባቢ ጊዜያዊ ሕክምና መስጫ ጭምር ተቋቁሞ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
ጊዜያዊ ሕክምና መስጫው ድንገተኛ ታመው ለሚመጡ እንግዶች አፋጣኝ ምርመራ እና ሕክምና ለመስጠት የታሰበ መኾኑን በሥራ ላይ አሚኮ ያገኛቸው የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ክሊኒካል ነርስ መላኩ ይርዳው ተናግረዋል።
ከበድ ያለ ችግር ካጋጠመ ደግሞ በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማት ሕክምና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ጤና
ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ዋና ኀላፊ እሸቱ ገስጤ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልን ለማክበር ወደ ላሊበላ የሚመጡ እንግዶችን ጤንነት ለመጠበቅ እንግዶች የሚያርፉበትን ቦታ የመለየት ሥራ መሠራቱን ገልጸውልናል።
እንግዶች ባረፉበት አካባቢ ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤት ተዘጋጅቶ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። 246 የሚኾኑ የጽዳት ሠራተኞችም ተመድበው የንጽሕና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፤ የመታጠቢያ እና የመጠጥ ውኃ አቅርቦትም ተዘጋጅቷል።
በአካባቢው የሚሸጡ ምግቦችን ደኅንነት የመከታተል እና የበሽታ የአሰሳ ቅኝት እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
በድንገት የታመሙትን ደግሞ በከተማዋ ጊዜያዊ የሕክምና መስጫ ድንኳን ጭምር ተቋቁሞ ነጻ ሕክምና እየተሰጠ ይገኛል።
ለዚህ ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ እና ጤና ሚኒስቴር የመድኃኒት እና የበጀት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በቀሪ ቀናትም እንግዶች ጤንነታቸው ተጠብቆ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
