
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከለካያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ባለፉት ሦሥት ወራት በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በተሠሩ የጸጥታ ሥራዎች ዙሪያ ከሥራ ኀላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። የቀጣይ የስምሪት አቀጣጫም ሠጥተዋል።
በውይይታቸውም የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እና በማንነቱ የሚኮራ ፣ የመረጠውን መንግሥት የሚወድ መኾኑን በተግባር ማረጋገጡን ገልጸዋል። ባዕዳን አስታጥቀው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የላኩትን ጽንፈኛ ዓላማ በመቀልበስ ሀገር ወዳድነቱን ማረጋገጡንም አንስተዋል።
የአዊ ብሔረሰብን ብሎም የጎጃምን ሰላም ማረጋገጥ የጠላቶቻችንን የትርምስ ፍላጎት መቀልበስ በመኾኑ ሕዝቡ እና የጸጥታ ኃይሉ በመቀናጀት በተደረጉት ኦፕሬሽኖች ጽንፈኛው ላይ ከፍተኛ ምት ማሳረፍ መቻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ” በሳምንት አዲስ አበባ እገባለሁ ” የሚለው ዲስኩር ተቀይሯል፤ ” ክልሉን አፍርሼ የፈለኩትን አደርጋለሁ ” የሚለው ክፍለ ዘመኑን ያላገናዘበ እብሪት ተቀልብሶ በኾነ ቀበሌ ላይ ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ ተደርጓል ነው ያሉት።
በተደረጉት ስምሪቶች በጽንፈኛው ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል። ጽንፈኛው ከፍተኛ የሎጀስቲክ እጥረት አጋጥሞታል፤ ኀይሉም ወደ ትንንሽ ቡድን ተበትኖ ቆሞ የመዋጋት አቀሙ መነጠቁን አስገንዝበዋል።
ከምሥራቅ እዝ ሚዲያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሪዎችም በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ስምሪት በመስጠት ፣ ሕገ ወጥ የሰው እና የመሳሪያ ዝውውርን ፣ ወደ ከተማ ሾልከው የሚገቡትን ፣ በዝርፊያ የተሰማሩትን በመቆጣጠር፣ የጸጥታ ኀይሉን አቅም በማጠናከር እና ሰላምን በማዳበር የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
