በሦስት ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል፡፡

154

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባለፉት ሦስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከኅብረተሰብ ተሳትፎ መገኘቱን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ገቢው የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ከተረጋገጠበት ካለፈው መጋቢት እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

የጽሕፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት ኅብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድቡ የሚያደርገው ተሳትፎ እየጨመረ ነው።

ለዚህ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ የተገኘውን ከ180 ሚሊዮን 950 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለአብነት አንስተዋል።

ገቢው በተለይ ከ”8100 A” እና ከቦንድ ግዥ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብሮች መገኘቱን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ችግር በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብሮች ማካሄድ በማይቻልበት ሁኔታ ይህ ገቢ ከኅብረተሰቡ መገኘቱ የሚያበረታታ እንደሆነም ነው የገለጹት።

ይህም ሕዝቡ ለሕዳሴ ግድቡ እውን መሆን ያለውን ቁጭትና ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አክለዋል።

ኅብረተሰቡ ግድቡን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት የኮሮናቫይረስ ተፅዕኖ ሳይገድበው ጤናውን እየጠበቀ ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። የአገሪቷን ሠላምና አንድነት በማስጠበቅና ሉዓላዊነትን በማጠናከር የመደጋገፍ ስሜቱ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

እስካሁን ሕዝቡ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተነግሯል።

የግንባታ አፈጻጸሙ 74 በመቶ የደረሰው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጪው ሐምሌ የውኃ ሙሌት እንደሚጀመር ይታወቃል፤ ለዚህ እንዲረዳም የደን ምንጣሮ ሥራው ተጀምሯል። የደን ምንጣሮው ከ32 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለት የሚከናወን እንደሆነም ታውቋል፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየመሠረተ ልማት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን በደባርቅ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ቦታ ባለቤት የሆኑ ነዋሪዎች ገለጹ።
Next articleሦስቱ ሀገራት ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ የአፍሪካ ኅብረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሙሳ ፋኪ መህማት አስታውቀዋል፡፡