የከፍታው ዘመን

6
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ1951 ዓ.ም ታኅሣሥ 20 በዚህ ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የመጀመሪያ ጉባኤ ለኢትዮጵያም ኾነ ለአፍሪካ ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ነበር።
ጉባኤው ተከፍቶ የተካሄደው በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር ሲኾን በወቅቱ የተመድ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዳግ ሀመርሾልድ ተገኝተው ነበር። የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አበበ ረታ የኮሚሽኑ የመጀመሪያው ሊቀመንበር ኾነውም ተመርጠዋል።
በወቅቱ አዲስ አበባ የኮሚሽኑ ቋሚ መቀመጫ እንድትኾን መመረጧ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት እና አንድነት የምታደርገውን ጥረት ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሰጠ ክስተት ነበር። በወቅቱ ኮሚሽኑ የተመሠረተው የአፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር፣ ማኅበራዊ ዕድገትን ለማምጣት እና በአህጉሪቱ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራ ለማልማት ነበር።
ለዚህ ታሪካዊ ተቋም ማቆያ ይኾን ዘንድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “አፍሪካ አዳራሽን” አስገንብተው በስጦታ መልክ ለኮሚሽኑ አበርክተዋል። ይህም አዳራሽ በኋላ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) የተመሠረተበት ስፍራ ኾኗል።
ይህ ክስተት አዲስ አበባ “የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መዲና” እንድትባል መሠረት የጣለ ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
✍ የመጀመሪያው የአውሮፕላን በረራ በኢትዮጵያ
ከ80 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውን ከአዲስ አበባ ተነሥቶ በአስመራ በኩል ወደ ካይሮ ግብጽ በረራ አድርጓል።
ድርጅቱ ታኅሣሥ 21/1938 ዓ.ም ተመሥርቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ በረራውን መጋቢት 30/1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነሥቶ ካይሮ ድረስ አከናወነ። አየር መንገዱ ሲመሠረት ከአሜሪካ ወታደራዊ ኀይል የተገዙ እና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት DC 3-C47 አውሮፕላኖች ነበሩት። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
✍ ገመድ አልባ ስልክ በኢትዮጵያ
ታኅሣሥ 26/1926 ዓ.ም በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ገመድ አልባ ስልክ አገልግሎት የተጀመረበት የታሪክ ምዕራፍ ነው። አገልግሎቱ የተጀመረው በአዲስ አበባ እና በጂቡቲ መካከል በነበረ የሬዲዮ ግንኙነት ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር የነበራት የግንኙነት ፍጥነት እንዲጨምር እና የዲፕሎማሲ እንዲሁም የንግድ ሥራዎች እንዲቀላጠፉ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ለዚህ አገልግሎት መሳካት በአቃቂ የተገነባው የሬዲዮ ማስተላለፊያ ጣቢያ ቁልፍ ሚናም ነበረው። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሀገሪቱን ለማዘመን ከነበራቸው ራዕይ አንዱ የኮሙኒኬሽን ዘርፍን ማስፋፋት በመኾኑ ለዚህ የገመድ አልባ ስልክ አገልግሎት መጀመር ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል። ይህ ጅማሮ የዛሬው የኢትዮ ቴሌኮም ዕድገት አንዱ መሠረት ተደርጎ ይወሰዳል። የኢትዮ ቴሌኮም ድረገጽን በመረጃ ምንጭነት ተጠቀምን።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleግጭትን አውግዘዋል፤ ለሰላም ተነስተዋል!
Next article“በቅንጅት በተደረጉት ኦፕሬሽኖች ጽንፈኛው ላይ ከፍተኛ ምት ማሳረፍ ተችሏል” ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ