የሌማት ትሩፋት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል እያገዘ ነው።

6

እንጅባራ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቻግኒ ከተማ የደለቡ የቁም እንስሳት እና የእንስሳት ተዋጽኦዎች ዐውደ ርዕይ ተካሂዷል።

የደለቡ የቁም እንስሳትን ለዕይታ ያቀረቡ የከተማው ነዋሪዎችም በዘርፉ ተጠቃሚ መኾናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።

ዐውደ ርዕዩ ምቹ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።

የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ይበልጣል ሰይድ የሌማት ትሩፋት የኑሮ ወድነትን፣ ሥራ አጥነትን እና በምግብ እጥረት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቅረፍ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ በአራት ክላስተሮች የቁም እንስሳት ማድለብ፣ የወተት ምርት እና የዶሮ እርባታ ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡

ዐውደ ርዕዩ ለሌሎች ልምድ ለማካፈል እና አምራቾችን ከሸማቾች ጋር በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑንም አንስተዋል።

በዘርፉ የሚነሱ የመኖ፣ የውኃ እና የመሥሪያ ቦታ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በሌማት ትሩፋት ላይ እየታዩ ያሉ አበረታች ለውጦች ለሰላም የተከፈለው ዋጋ ውጤቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ድህነትን ማሸነፍ ቁልፍ አጀንዳ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ፀር የኾኑ ድህነት እና ጽንፈኝነትን በጋራ መታገል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲ አንድን ሀገር ለማሻገር የሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮች መኾናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈባቸው ተስፋን ወደ ዕውንነት የቀየሩ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

ሁሉም በየተሰማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት የሀገሪቱን ዕድገት ማፋጠን ይገባዋል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ሰላም እና ልማት ለማደናቀፍ የሚታትሩ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን አደብ ለማስገዛት እየሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም አማራጭ የተቀበሉ ኀይሎች ዘላቂ የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ ይሠራል።
Next articleግጭትን አውግዘዋል፤ ለሰላም ተነስተዋል!