
ከተማ አስተዳደሩ የአስተዳደር ወሰኑን ችግር በመፍታት በሚቀጥለው በጀት ዓመት መሠረተ ልማት እንደሚያሟላላቸው አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በግለሰብ ደረጃ 12 ሺህ ብር የሊዝ እና የአርሶ አደር የካሳ ክፍያ ከፍለው የመኖሪያ ቤት በገነቡበት ቦታ አርሶ አደሮች “የተሟላ የካሳ ክፍያ አልተከፈለንም” በሚል የመተላለፊያ መንገዶችን ጭምር እንደዘጉባቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ 12 ማኅበራት የመኖሪያ ቤት ቦታ ተጠቃሚ መሆናቸውን አባላቱ ነግረውናል፤ ነገር ግን 296 አባዎራዎች እስከ 700 የሚደርሱ የቤተሰብ አባላት መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ እና መሰል የመሠረተ ልማት ባልተሟላለት ሥፍራ ለመኖር መገደዳቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ለከተማ አስተዳደሩም ጥየቄ አቅርበው እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡ የመኖሪያ አካባቢው በወንዝ የተከበበ በመሆኑ ድልድይ ባለሠራቱም በክረምት ወቅት እንደሚቸገሩ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ቦታ ችግራቸውን መፍታቱ መልካም መሆኑን ገልጸው መሠረተ ልማቱም እንዲሟላ ጠይቀዋል፡፡
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዳለ ደምሴ እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ ዙሪያ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎች የፕላን ወሰናቸው በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን አስተዳደራዊ ወሰናቸው በዙሪያ ወረዳው በመሆኑ ለማስተዳደር አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።
እናም ቀበሌዎቹ በከተማ አስተዳደሩ እንዲካተቱ ጥያቄው ለዞንና ለክልል መቅረቡን ከንቲባው ገልጸዋል፤ በ2013 በጀት ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ተካትተው የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንደሚፈቱላቸውም ከንቲባው አስታውቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወርቁ ለምለሙ ደግሞ በቀበሌዎቹ ውስጥ የሚኖረው የሕዝብ፣ የተቋማት ብዛት እና የበጀት መጠን ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፤ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ለክልሉ መንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እንዳገኘ ችግሩ እንደሚፈታ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡