የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ኀይሎች ዘላቂ የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ ይሠራል።

17

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል የአሥተዳደር ዘርፍ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ አካሂዷል።

‎‌በመድረኩ የአማራ ክልል አሥተዳደር ዘርፍ ሥር የሚገኙ ተቋማት ያለፉት ስድስት ወራት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

‎‌ተቋማቱ በግማሽ ዓመቱ ያከናወኗቸውን ተግባራት አፈጻጸም ከግቦች አኳያ፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል። የቀረበውን ሪፖርት መሠረት በማድረግም ውይይት ተካሂዷል፡፡

‎የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የአሥተዳደር ዘርፍ መሳካት ለሌሎች ዘርፎች ስኬታማነት ያለው ሚና በደንብ መታየት አለበት ብለዋል፡፡

የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ለሰላም እና ለምርታማነት ጠቀሜታው የጎላ በመኾኑ አባላቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

‎‌የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ለኅብረተሰቡ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት በተደራጀ መንገድ መሠራቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

‎አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡም ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የሰላም ዕጦት ክልሉን እየጎዳው በመኾኑ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በመቀናጀት መሠራት አለበት ነው ያሉት፡፡

‎‌የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም እና ልማት የማረጋገጥ ሥራ ለማስቀጠል የዘርፉ ሚና ከፍተኛ በመኾኑ በቅንጅት መሠራቱ ለተሻለ ውጤት ያበቃል፤ የክልሉ መንግሥትም ዘርፉን ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፈው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

‎‌በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) በዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ ተግባራት በፍትሕ ዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩ፣ ክልሉ ከነበረበት አደጋ ፈጥኖ ወጥቶ በማንሰራራት ላይ መኾኑ፣ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ከሃይማኖት ተቋማት ጋር መሠራቱን በጥንካሬ አንስተዋል፡፡

‎የሚሊሻ መዋቅሩ በመጠናከሩ የሕግ ማስከበር አቅም መሻሻሉ እና ሙስናን በመታገል የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መልካም መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ኀይሎችን አሠራሮችን በመዘርጋት ዘላቂ የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ማድረግ፣ በሙስናው ዘርፍ ተጨባጭ ጥቆማወችን ይዞ ከፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት እና ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መሠራት እንዳለበት አስተባበሪው አመላክተዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሥልጠና ያገኙትን አቅም በመጠቀም ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠሩ ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት ተናገሩ።
Next articleየሌማት ትሩፋት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል እያገዘ ነው።