በሥልጠና ያገኙትን አቅም በመጠቀም ሰላምን ለማጽናት እንደሚሠሩ ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት ተናገሩ።

33

እንጅባራ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት በአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በጥሩ ብርሃን መሠረታዊ የፖሊስ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ያሠለጠናቸውን የሰላም አስከባሪ አባላት አስመርቋል።

ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላትም በቆይታቸው ወታደራዊ አቅምን የሚያሳድጉ የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ሥልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

በሥልጠና ያገኙትን አቅም በመጠቀም የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ሰላም ለማጽናት ቁርጠኛ መኾናቸውን
አስረድተዋል።

በአማራ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጥሩ ብርሃን መሠረታዊ ፖሊስ ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ ኮማንደር ይሰማ ተናኘ እንዳሉት የዛሬ ተመራቂ ሰላም አሰከባሪዎች ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ሥልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ናቸው።

ተመራቂ ሰላም አስከባሪዎች በዓላማ ጽናት፣ በታማኝነት እና ቁርጠኝነት ኅብረተሰቡን ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም አሳሰበዋል።

የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን አማካሪ ጎሹ ስንቴ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ በሥልጠና የበቃ ሠራዊት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት የመፈፀም አቅምን ያጎለበቱ፣ በአካል እና በወታደራዊ ሥነ ልቦና ዝግጁ የኾኑ መኾናቸውን አንስተዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ወቅቱ የኢትዮጵያን ዕድገት እና አንድነት የማይመኙ የውስጥ ባንዳዎች እና የውጭ ባዳዎች እንቅልፍ ያጡበት መኾኑን ተናግረዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች የእነዚህን ጸረ ሰላም ኀይሎች እኩይ ሴራ በማምከን ዘላቂ ሰላም ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም መኾናቸውንም ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ተመራቂ የሰላም አስከባሪ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ኅብረተሰቡን ሰላም የሚነሱ ጸረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን በመመከት የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ታሪካዊ ኀላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመንገድ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን ቁልፍ ጉዳይ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየሰላም አማራጭ የተቀበሉ ኀይሎች ዘላቂ የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ለማድረግ ይሠራል።