“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምናደርገው ርብርብ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ይኾናል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

23

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።

በዛሬው ውይይት ላይ የተሳተፉት ተቋማት በለውጥ አስተሳሰብ የተካተቱና የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉም የተካተቱበት መኾናቸውን ገልጸዋል። በጋራ ከምናከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ በየተቋሞቻቸው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በምናደርገው ርብርብ የማይተካ ሚና አላቸው ነው ያሉት።

አዲሱ ምክር ቤት በአዲሱ ፖሊሲ፣ አዋጅ እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ላይ በመመስረት፤ የሕዝብን አቅም በማስተባበር የማይበገር ማኅበረሰብ ለመገንባት እና የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ አደጋዎችን ጉዳት በቀነሰ መልኩ ለመከላከል በትጋት ይሠራል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ሥርዓታዊ እና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም በስብሰባችን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት። ከ2016 ዓ.ም ክረምት ጀምሮ በተቀረጹ ፍኖተ ካርታዎች መሠረት ልመና እና ተረጂነትን በምርታማነት ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ፤ ውጤትም እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በዘላቂነት አስተማማኝ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መገንባት፣ የመጠባበቂያ ክምችትን በፌደራል እና በክልሎች ማደራጀትና ተፈናቃይ ዜጎቻችን በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ አምራችነት እንዲመለሱ ማድረግ የመንግሥታችን ዋነኛ ግብ ነው።

በተለይም የማኀበረሰባችንን የመደጋገፍ መልካም ልምምድ እና የአጋርነት እሴት በማጎልበት በየአካባቢያችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምናደርገው ርብርብ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ይኾናል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ጉዟችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዕውቀትና በጥበብ መሻገርን ይጠይቃል። ይህንንም በመደመር ዕይታና በጠንካራ አመራር ለማሳካት ከስምምነት ላይ ደርሰናል ነው ያሉት።

የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደ ሀገር መላውን ማኅበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበዓል ገበያ በፍኖተሰላም ከተማ
Next article“የመንገድ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን ቁልፍ ጉዳይ ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ