
ፍኖተሰላም: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተሰላም ከተማ የልደት በዓል የእንስሳት ገበያን በተመለከተ አሚኮ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሻጭ እና ገዥዎች በገበያው የተሻለ አቅርቦት መኖሩን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በቂ አቅርቦት መኖሩንም ያስረዱት አስተያየት ሰጭዎቹ ነገር ግን መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አስረድተዋል።
የዋጋ መጨመሩ ዋነኛ ምክንያት የእንስሳት መኖ ዋጋ መናር መኾኑን ሻጮች አብራርተዋል።
በግ ሲገዙ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጭዎች እንደገለጹት በግ ከ7ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው። ከዚህ በፊት ከነበረው የበዓል ገበያ መጠነኛ የዋጋ መቀነስ መኖሩንም ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ አርሶአደሮች፣ በግል እና በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች 1ሺህ 600 ሰንጋዎች እና ከ2ሺህ በላይ በጎች ለገበያ ማቅረባቸውን የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ላቀው ኑርልኝ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
በገበያው የእርድ እንስሳት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ሲሠራ መቆየቱንም አንስተዋል።
በተለይ አካባቢው በርካታ የእንስሳት ሃብት ያለበት እና ያለፉት ወራት ለማድለብ ምቹ ሁኔታዎች በመኖራቸው በቂ የእንስሳት አቅርቦት መኖሩን አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
