
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ኀይሎች እና የፓሊስ ሠራዊት ማኅበራት ኅብረት አባላት በደርግ ዘመነ መንግሥት እና ቀደም ብሎ በነበረው ሥርዓት በአየር ኀይል፣ በምድር ጦር፣ በባሕር ኀይል እና በፖሊስ ሠራዊትነት ያገለገሉ ናቸው።
ደርግ ከወደቀ በኋላ ጦሩ በመበተኑ ብዙዎች የከፋ ችግር ያስተናገዱ ናቸው። ከደርግ ውድቀት በኋላም የተደረገላቸውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብለው በሀገራዊ ግዳጅ በርካቶች ተሳትፈዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ኀይሎች እና የፖሊስ ሠራዊት ማኅበራትም በቅርቡ ኅብረት መሥርተዋል።
ኅብረቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተመሠረቱ የቀድሞ የጦር እና የፖሊስ አባላት ማኅበራትን ያካተተ ነው።
የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ኀይሎች እና የፖሊስ ሠራዊት ማኅበራት ኅብረት በሥሩ ያሉ አባላት ሕክምና፣ መኖሪያ ቤት እንዲሁም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን የኅብረቱ ምክትል ሠብሣቢ ሻለቃ ማሞ እሸቱ ተናግረዋል።
የቀድሞ የሠራዊት አባላት ለሀገራቸው ሕይወታቸውን የሰጡ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ እና ደማቸውን ያፈሰሱ በመኾናቸው የበለጠ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ኅብረቱ ጥረት እያደረገ መኾኑን ምክትል ሠብሣቢው ገልጸዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ኀይሎች እና የፖሊስ ሠራዊት ማኅበራት ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤውንም አካሂዷል።
ዘጋቢ፦ ተመስገን ዳረጎት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
