
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሃባሪ መዲካል ፕላዛ የተሰኜ የጤና ተቋም በአዲስ አበባ ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸው ለሀገር እና ወገን የሚቆረቆሩ ተቋማት እንዳሉ የሃባሪ ሜዲካል ፕላዛ ማሳያ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ በሀገር ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ መንግሥት ይደግፋል ብለዋል፡፡ “በጋራ እና በትብብር በመሥራትም አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል እናደርጋታለን” ነው ያሉት፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ መንግሥት ብቻውን የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ስለማይችል ከግል ዘርፉ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የሃባሪ ሜዲካል ፕላዛ በትብብር መሥራት ምን ያህል መልካም ውጤት እንዳለው ማሳያ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትፘ የጤና ባለሙያዎቹ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ሲሰጡ በሙሉ ታማኝነት እና ኀላፊነት መኾን እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የሃባሪ መዲካል ፕላዛ መሥራች እና ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዶክተር አከዘ ጣመ የጤና ተቋሙ በሀገሪቱ በአይነታቸው የመጀመሪያ የኾኑ የጤና አገልግሎቶች የሚሰጡበት እና አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ ሂደት ጉልህ ድርሻ የሚወጣ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ሃባሪ ሜዲካል ፕላዛ 15 ስፔሻሊቲ እና ሰብ ሰፔሻሊቲ ያሉት እና የ”ቪአይፒ” አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ዜጎች ወደ ውጭ በመሄድ ለሕክምና በዓመት የሚያወጡትን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ንዋይ በማስቀረትም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
