“አደጋ ሊጥል የሚመጣን ኃይል በመመከት ሕግ ማስከበር አለባችሁ” ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ

20

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአማራ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ጥሩ ብርሃን መሠረታዊ የፖሊስ ማሠልጠኛ ኢኒስቲትዩት ያሠለጠናቸውን የሰላም አስከባሪ አባላት አስመርቋል።

ተመራቂዎች በቆይታቸው ፣ የወታደራዊ አካል ብቃት ፣ ተኩስ ፣ የውጊያ ስልት ፣ የሽምቅ እና ጸረ ሽምቅ ውጊያ ፣ የወታደራዊ ሰልፍና ሰላምታ ፣ የስነልቦና ግንባታ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸው ተገልጿል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በሀገር መከለካያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ውትድርና የሀገርን ሉዐላዊነት እና የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅ መተኪያ የሌላትን ሕይወት የሚከፈልበት መኾኑን ገልጸዋል።

ሀገርን ከውጭ ወራሪ እና ከውስጥ ጸረ ሰላም ለመጠበቅ የሚያገለግሉበት ክቡር ሞያ ነው ብለዋል።
ዜጎች የሀገራቸው ሰላም ፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ ገድል የሚፈፅሙበት የጀግኖች መገኛ መኾኑንም ገልጸዋል።

የዚህ ጀግና ሠራዊት አካል ኾናችሁ ሀገራችሁን ለማገልገል በመቀላቀለችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል ነው ያሉት።

በየቦታው ባንዳዎች የለኮሱትን እሳት እየተፋለሙ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ እና ገናናነቷን ለማስቀጠል ጀግንነት እየፈጸሙ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የዛሬ ተመራቂዎችም በአካባቢው አደጋ ሊጥል የሚመጣን ኃይል በመመከት ሕግ ማስከበር አለባችሁ ነው ያሉት።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የዞኑን ሰላም እንዲያስከብሩ ተመልምለው የሠለጠኑ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተመራቂዎች ብሔረሰብ አሥተዳደሩን እና ክልሉን ከፅንፈኞች በማፅዳት ግዳጃቸውን በስነ ምግባር እና በቁርጠኝነት እንዲፈፅሙም አሳስበዋል ።

ተመራቂዎችም የተሰጣቸውን ሥልጠና በተግባር በማዋል ሰላም እንደሚያስከብሩ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“‎በተከፈለ መስዋዕትነት ክልሉ ተደቅኖበት ከነበረው አደጋ ወደ አንጻራዊ ሰላም ተመልሷል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)
Next articleየጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከግል ዘርፉ ጋር በትብብር መሥራት ያስፈልጋል።