“‎በተከፈለ መስዋዕትነት ክልሉ ተደቅኖበት ከነበረው አደጋ ወደ አንጻራዊ ሰላም ተመልሷል” አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)

56

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የአማራ ክልል የአሥተዳደር ዘርፍ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

‎በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እና የመንግሥት አሠራር መዋቅሩን ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት ስድስት ወራት ሌት ከቀን ለሠሩ እና ላሥተባበሩ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።

“‎በተከፈለ ውድ መስዋዕትነት ክልሉ ተደቅኖበት ከነበረው አደጋ ተላቆ ወደ አንጻራዊ ሰላም ተመልሷል” ብለዋል። ይህ ሁኔታ ወደ ዘላቂ እና የማይቀለበስ ሰላም እንዲደርስ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት።

‎የአሥተዳደር ዘርፍ ተቋማት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የነበረውን ጉዞ መፈተሽ ስኬቶችን ለማጽናት እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል።

‎የአሥተዳደር ዘርፉ የክልሉ የትኩረት ማዕከል ነው ያሉት አሥተባባሪው በዚህ የሚመሩ ተቋማት ደካማ ከኾኑ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ይሸረሽራል፣ ሰላም ይጠፋል፣ ልማትም ይቆማል ብለዋል።

‎ሰላም በሌለበት ትምህርት የለም፣ ፍትሕ በሌለበት ንግድ እና ኢንቨስትመንት አይታሰብም፤ በመኾኑም በግምገማው ከቁጥር ሪፖርት ባለፈ የሕዝቡን እርካታ ምን ያህል ተረጋግጧል፤ የክልሉ ሰላም ምን ደረጃ ላይ ደርሷል የሚለው የሚገመገምበት መድረክ መኾኑን ተናግረዋል።

‎ባለፉት ስድስት ወራት በፍትሕ እና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት ፍትሕ በክልሉ ለዜጎች የተረጋገጠ መኾኑን በተግባር ማሳየት ተችሏል ነው ያሉት።

‎በፍትሕ፣ በጸጥታ እና በሚሊሻ መዋቅሩ በቆራጥነት እና በወገንተኝነት በከፈሉት መስዋዕትነት የክልሉ የጀርባ አጥንት መኾናቸውን አስመስክረዋል ብለዋል።

‎በጸረ ሙስና እና በመልካም አሥተዳደር ተግባራት በርካታ ችግሮች ቢታለፉም አሁንም የሥርዓቱ ችግሮች እና ካንሰር መኾናቸውን ሕዝቡ በየመድረኩ ያነሳል ብለዋል።

‎በማረሚያ ቤቶች ከቅጣት ማዕከልነት ባሻገር የስብዕና ግንባታ እና ምርታማ ዜጎችን የሚያመረቱ እንዲኾኑ ለማድረግ ተግባራት ይታያሉ ነው ያሉት።

‎ሰላም የሚጸናው በውስጥ ብቻ ባለ ሰላም ሳይኾን ከጎረቤት ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥቱ አካላት ጋር በሚኖር ትብብር በመኾኑ በበይነ መንግሥት ግንኙነት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ውይይት ይካሄዳል ነው ያሉት።

‎ውይይቱ እያንዳንዱ ተቋም የሌላውን ተቋም ሥራ በተገቢው መንገድ በመገንዘብ እና በቅንጅት በመሥራት በክልሉ ውስጥ ፍትሕ እና ሰላም እንዲመጣ ሚና አለውም ብለዋል።

‎ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጎንደር ከተማ በበሽ ጥቅል ዕድለኛዋን ሸለመ።
Next article“አደጋ ሊጥል የሚመጣን ኃይል በመመከት ሕግ ማስከበር አለባችሁ” ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ