ግብይት በላሊበላ!

8

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ የግብይት ሥርዓቱ ከሚነቃቃባቸው ወቅቶች ውስጥ ታኅሣሥ እና ጥር ወራት ይገኙበታል።

በእነዚህ ወቅቶች የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት እና የጥምቀት በዓላትን ተከትሎ በተለይም የባሕል አልባሳት እና የቅርጻ ቅርጽ ውጤቶች ይበልጥ ተፈላጊዎች ናቸው።

ከ20 ዓመት በላይ በባሕል አልባሳት እና ቅርጻ ቅርጽ በመሸጥ ላይ እንደቆዩ ለአሚኮ የተናገሩት ሀዳስ ቀጸላ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የግብይት ሥርዓቱ ተዳክሞ መቆየቱን ገልጸውልናል።

በዚህ ዓመት በተለይም ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ደግሞ የገበያ ሁኔታው መነቃቃት ማሳየቱን ነው የተናገሩት።

በተለይም ደግሞ የባሕል አልባሳት፣ ከሸክላ እና ከእንጨት የተሠሩ ባሕላዊ ቅርጻ ቅርጾች እና የተለያዩ ጌጣጌጦች በውጭ ጎብኝዎች ተፈላጊ እንደኾኑም አንስተዋል።

ከአንጎት ወረዳ በበዓሉ ላይ የተለያዩ የሃይማኖት መገልገያዎችን ለገበያ ለማቅረብ ወደ ላሊበላ እንደ መጡ የገለጹት መሪጌታ እያሱ ቢሰጠኝ የአባቶችን ካባ፣ የሃይማኖት መጽሐፍት እና የባሕል አልባሳትን ለግብይት አቅርበው ተመልክተናል።

አሁን ላይ በላሊበላ ያለው የግብይት ሁኔታ ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሃይማኖታዊ አልባሳትን ለገበያ በማቅረብ ግብይት ሲፈጽሙ ያገኘናቸው ሌላኛው ነጋዴ ቃለጽድቅ ምክር እንዳሉት ደግሞ ከዚህ በፊት በነበረው የሰላም ችግር ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ፈተኝ አድርጎት ቆይቷል።

አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር ተያይዞ የንግድ እንቅስቃሴው መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

የባሕል አልባሳትን ሲገዙ አሚኮ ያነጋገራቸው የውጭ ጎብኝ እንደገለጹት ገበያ የሚቀርቡ አልባሳት እና የቅርጻ ቅርጽ ውጤቶች ውብ፣ ማራኪ፣ የኢትዮጵያውያንን ቀለም ይበልጥ የሚያሳዩ እና ባሕልን የሚያሳድጉ ናቸው።

ይህንን ይበልጥ ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የማነብርሃን አባቡ እንዳሉት አካባቢው በኮሮና እና በተከታታይ በተከሰተው የጸጥታ ችግር የንግድ እንቅስቃሴው ተዳክሞ ቆይቷል።

በዚህ ዓመት በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም የንግድ እንቅስቃሴው መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።

በተለይም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ጋር ተያይዞ የባሕል አልባሳት እና የቅርጻ ቅርጽ ውጤቶች ይበልጥ ተፈላጊ መኾናቸውን ነው የገለጹት።

በዚህ ወቅት ማኅበረሰቡ የተሻለ ተጠቃሚ የሚኾንበት ወቅት መኾኑንም አንስተዋል።

ሕገ ወጥነት እና የዋጋ ንረት እንዳይኖር ክትትል እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበትራፊክ አደጋ ምክንያት እየገጠመ ያለውን ማኅበራዊ ቀውስ ለመቀነስ እየተሠራ ነው።
Next articleሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በጎንደር ከተማ በበሽ ጥቅል ዕድለኛዋን ሸለመ።