
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሩዋንዳ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በዋና ከተማዋ ኪጋሊ አንዳንድ አካባቢዎች ከትናንት ምሽት ጀምሮ ለ15 ቀናት የእንቅስቃሴ እገዳ ማስተላለፉን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዋና ከተማዋ ኪጋሊ በተደረገ አሰሳ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትሎ በስድስት መንደሮች ውስጥ የመንቀሳቀስ እገዳ ተጥሏል፡፡ በመንደሮቹ ለጤና አገልግሎት እና ለአስቸኳይ ጉዳዮች ብቻ ከተፈቀደላቸው ሰዎች በስተቀር ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በመንደሮቹ ያሉ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ሠራተኞችም በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡
በከተማዋ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ተጨማሪ የአሰሳ ጥናት ሌሎች የኪጋሊ ከተማ መንደሮች ተጋላጭነት እየታዬ እግዳው በሌሎች መንደሮች ላይም ሊተገበር እንደሚችል ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል፡፡
ሀገሪቱ ባለፉት ቀናት አዲስ የኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎችን እያገኘች መሆኑን ያስታወቀው የጤና ሚኒስቴር አራት የኪጋሊ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ 20 ሰዎች ትናንት በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን አመልክቷል፡፡ እንደ ሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ በአጠቃላይ በሀገሪቱ እስከ ትናንት 850 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ታውቋል፡፡
በግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡