የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የሲስተም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ።

7

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የሲስተም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጭነት በታኅሣሥ 23/2014 ዓ.ም የተጀመረው የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በዓመት እስከ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

​ሀገርን በመገንባት ሂደት በእውቀት የበለጸጉ ዜጎች ሚና የላቀ ነውና የዘመኑ የእውቀት ማዕከላትን ማብዛት ያስፈልጋል። የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት የዘመነ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ግባቶችን ወደ ሥራ አስገብቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሐ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ቤተ መጻሕፍቱ የሚሰጠው አገልግሎት ምቹ፤ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ይኾን ዘንድ የተቀናጀ የቤተ መጻሕፍት አሥተዳደር ሥርዓት፤ ዲጅታል ቤተ መጻሕፍት እና የምርምር ቤተ መጻሕፍት በሲስተሙ ውስጥ ተካተው ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

አንባቢያን የእውቀት ማዕከሉን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት፤ እንዲጠብቁት እና የሚያገኙትን እውቀት እና ግንዛቤ ደግሞ ለሀገር እና ወገን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን ታሪኩ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የተጀመረው ማዕከሉ በርካታ ተማሪዎችን ግንዛቤያቸውን በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና ሲጫወት መቆዬቱን ተናግረዋል።

አገልግሎቱን ለማዘመን የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተካተውበት ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ የእውቀት ብርሃን ያበራ የዕውቀት ቤት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleበላይ ጋይንት ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።