የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

16

 

ጎንደር: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ በከተማ አሥተዳደሩ የሰላም ጥሪውን ለተቀበሉ አካላት የክህሎት ማስጨበጫ ሥልጠና በመስጠት በማኅበር ተደራጅተው ሕይወታቸውን ይመሩ ዘንድ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጿል።

መምሪያው በጎንደር ከተማ አዘዞ ክፍለ ከተማ በከብት ርባታ ያደራጃቸውን 46 የቀድሞ ታጣቂዎችን ላቀፉ ሰባት ማኅበራት የመሥሪያ ቦታ አስረክቧል።

በመስሪያ ቦታ ርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ አካሌ ፀጋየ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ከማቋቋም አንፃር ተቋሙ የመሥሪያ ቦታ፣ የብድር አገልግሎት፣ ሥልጠና እና መሰል ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሥራ እድል ፈጠራው በሌሎችም ክፍለ ከተሞች ተጠናከሮ የሚቀጥል መኾኑንም ተናግረዋል።

የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወንድወሰን ተስፋየ በበኩላቸው የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለመጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን የሥራ ዕድል መፍጠርን ቁልፍ ተግባር አድርገው እየሠሩ መኾኑን ጠቅሰዋል።

የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ከገቡት መካከል ወጣት ወንዴ አያሌው አንዱ ነው። የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በመግባቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል። መንግሥት እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል። ያገኘውን የማልማት እድል ተጠቅሞ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ዝግጁ መኾኑን ገልጿል።

ሌላው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡት አወቀ ምትኩ መንግሥት በቃል የሚናገረውን በገሃድ እያሳየ መኾኑን አይተናል በሚል የተደረገውን ድጋፍ አወድሰዋል።

በተደራጁበት የሥራ ዘርፍ ራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ ለሸማቾችም ግብዓት የሚኾን ምርት ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልጿል።

ዘጋቢ:- ማርታ አዱኛ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከ2 ትረሊዮን ብር በላይ ኾኗል።
Next article“አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ የእውቀት ብርሃን ያበራ የዕውቀት ቤት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ