ከደባርቅ-በለስ- መካነ ብርሃን ድረስ የሚገነባው የመንገድ ሥራ ምን ላይ ደረሰ

12

 

ደባርቅ: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከደባርቅ፣ በለስ፣ መካነ ብርሃን የሚገነባው የ102 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት እንዲሳለጥ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደጉ የደባርቅ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የመንገድ ሥራው ባለመጠናቀቁ ምክንያት ለጎርፍ፣ ለነፋስ እና ለሌሎች መሰል ችግሮች ተጋላጭ ኾነው መቆየታቸውን ነዋሪዎቹ አብራርተዋል።

የመንገድ ሥራው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ካልገባ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ሥራው እንዲሳለጥ ከተማ አሥተዳደሩ እያደረገው ያለው ተግባር የሚበረታታ መኾኑን አመላክተዋል።

በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቱ ሥራ አሥኪያጂ ተስፋ ዘለቀ ከደባርቅ፣ በለስ፣ መካነ ብርሃን 102 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ሥራ ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከደባርቅ ቧሂት ያለው 63 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ በአሁኑ ወቅት 7 ነጥብ 5 በመቶ የደረሰ ሲኾን ከበለስ መካነ ብርሃን ያለው 39 ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ 78 በመቶ መጠናቀቁን አመላክተዋል።

መንገዱን በፍጥነት ሠርቶ ለማጠናቀቅ የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ቦታዎችን ከሦስተኛ ወገን ማጽዳቱ እና የማኅበረሰቡ በጎ ተነሳሽነት እንደሚያግዛቸውም ገልጸዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ በመንገድ ፕሮጀክቱ የደባርቅ ከተማን የሚነካ ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ከሦስተኛ ወገን የማጽዳት ሥራ መከናዎኑን ተናግረዋል።

ከተማ አሥተዳደሩ የመንገድ ሥራው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ማኅበረሰቡ ከዚህ በፊት ይደርስበት ከነበረው ችግር እንዲወጣ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላልኝ አምሳሉ የመንገድ ሥራው አራት ወረዳዎችን የሚያገናኝ እና 102 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ፕሮጀክት መኾኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ሥራው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ መሬትን ከሦስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ እና የግንባታ ሥራውን በማሥተባበር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዘላቂ ሰላምን እና ልማትን ለማረጋገጥ ሕዝቡ ፅንፈኞችንና ተላላኪወችን የሚሸከምበት ትክሻ እንደሌለው በሕዝባዊ የውይይት መድረኮች አረጋግጧል ” የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
Next articleአዋሽ ባንክ በደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ አረጋውያን እና አቅመ ደካማ ወገኖች 900 ሺህ ብር የሚገመት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ።