
ደብረ ብርሃን፡ ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት ተቋማቶች “ግጭቶች መቆም አለባቸው ለሰላም ሁላችንም ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ጥሪ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ መንግሥት የሰላም በሩን ክፍት አድርጎ በሆደ ሰፊነት ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ እያሳየ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በርካታ ወንድሞች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰባቸው እየተቀላቀሉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ወርቃለማሁ የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ እንዲሠሩም አሳስበዋል።
ምክትል ከንቲባው የትላንት አባቶች በአባትነት እና በመሪነት ጥበብ ሀገር ፀንታ እንድትቆም አድርገዋል፤ ዛሬም የሃይማኖት አባቶች የሰላም ሃዋርያ በመኾን ለዘላቂ ሰላም ልትተጉ ይገባል ብለዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የሰልፉ ተሳታፊዎች የሰላም ዋጋ ውድ ነው፤ ለሰላም ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል ነው ያሉት።
ሁሉም የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም አማራጭ መጥተው ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን፣ ፍቅርን እና አንድነትን ያስተሳስሩ ገመዶች ናቸው፤ ቤተ ዕምነቶች ከሰላም ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው የሰላም ምንጮች ናቸው የሚሉ በሰልፉ ላይ የተስተጋቡ መልዕክቶች ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
