
ደባርቅ፡ ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የሪፎርም እና የጂኦ-ስትራቴጂክ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።
በመርሐግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ እንደ ክልል ያጋጠመውን የሰላም እጦት ለመቀልበስ፣ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት የፖሊስ አባላት የላቀ አበርክቶ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
ውስጣዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እና ሕግ የማስከበር ርምጃዎችን በማጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሥልጠናው አጋዥ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ የተረዳ እና የተሻለ የመፈጸም አቅም ያለው የፖሊስ ሠራዊት አባላትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ምኅረት መለሰ ሥልጠናው በርካታ ጉዳዮችን የሚዳስስ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
ሥልጠናው የአባላቱን የግንዛቤ አቅም ለማሻሻል እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የፖሊስ ሠራዊት አባላቱ ከሥልጠናው በኋላ ሥነምግባራዊ መርኾዎችን በማክበር እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ሥልጠናው ግንዛቤን ከማዳበር ባለፈ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
ከሥልጠናው በኋላ ያገኙትን ዕውቀት እና ልምድ በመጠቀም የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኀላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ለመፈጸም እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
