
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) ሱዳን ሽግግሯን እየፈተነ የሚገኘውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ ለመፍታት የሚረዳ የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አግኝታለች፡፡ በጀርመን አዘጋጅነት በተካሄደ ኮንፈረንስ የተሳተፉ ለጋሽ አካላት ናቸው ድጋፉን ያደረጉት፡፡
የአውሮፓ ኅብረት 350 ነጥብ 13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ አሜሪካ 356 ነጥብ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፣ ጀርመን 150 ሚሊዮን ዩሮ፣ ፈረንሳይ 100 ሚሊዮን ዩሮ እና እንግሊዝ 150 ሚሊዮን ፓውንድ ለሱዳን ሰብዓዊ ድጋፍና ለልማት ግቦች መደገፊያ እንዲውል ለግሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለግሳ የነበረቸው ሳዑዲ ዐረቢያ 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና የተባበሩት ዐረብ ኤመሬት 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሱዳንን ሽግግሯን እንድታሳካ መደገፋቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡ ሁለቱ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት አልበሺር ከስልጣን እንደወረዱ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመደገፍ ቃል ገብተው እንደነበር ቢታወቅም ምን ያህል ቃላቸውን እንደፈጸሙ የታወቀ ነገር የለም፡፡
ቻይና እና ስፔንም 56 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ድጋፍና የዕዳ ስረዛ እንዳደረጉ ይታወሳል፡፡
የሱዳንን ሽግግር እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ለጋሽ አገራትና ተቋማት እንዲረዷቸው ከዚህ ቀደም መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
በአብርሃም በዕውቀት
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡