
ወልድያ: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግሎት በወልድያ ከተማ ለተመረጡ ሁለት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መምህራን የዐይን እና የጆሮ ሕክምና ድጋፍ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ቢኾን (ዶ.ር) ድጋፉ ከዐይን እና ጆሮ ሕክምና እና ልየታ ጀምሮ እስከ ሙሉ የጆሮ እጥበት እና የእይታ መርጃ መነፅር መኾኑን ገልጸዋል።
የጁ አልማ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዲስ በመኾኑ እና መሀል መቻሬ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ስለደረሰበት ዩኒቨርሲቲው ለድጋፍ እንደመረጣቸው ተናግረዋል።
በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ለ529 ተማሪዎች እና መምህራን የልየታ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል።
ረጅም ጊዜ በወሰደ ተደጋጋሚ የሕክምና ክትትል 65 መምህራን እና ተማሪዎች ተለይተው የመነፀር፣ የመድኃኒት እና የጆሮ እጥበት ድጋፍም ተደርጎላቸዋል።
18 የጆሮ እጥበት የሚያስፈልጋቸው እና 23 የእይታ መነፅር የሚያስፈልጋቸው ተለይተው ተጠቃሚ ሲኾኑ ቀሪዎቹ የዐይን ሕክምና መድኃኒት ድጋፍ አግኝተዋል።
ይህ ክትትል እና ድጋፍ ቀጣይ መኾኑን ያስረዱት ዳይሬክተሩ ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ላይ የተከሰተውን ስብራት ለማከም ከታዳጊ ተማሪዎች እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ማድረግ፣ የአይሲቲ ድጋፍ፣ የመምህራን የአቅም ግንባታ እና መሰል ድጋፎችን ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሕክምና ክትትልና ድጋፉ ላደረገው ትብብር አመስግነዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ የኾኑ የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው የማየት ችግርን በምርመራ መረዳታቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ባደረገው የሕክምና ልየታ ልጆቻቸው የድጋፍ መነፀር ተጠቃሚ በመኾናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
