ኢትዮጵያውያን የመጣንበት የግጭትና የጦርነት አዙሪት በቃን የምንልበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው።

9
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በጋራው መልዕክት ምክክር ለጋራ አሸናፊነት፣ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መኾኑን አንስቷል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ያለመግባባት፣ የንትርክ እና የእርስ በርስ ግጭት ምንጭ የነበረው ኋላቀር የፖለቲካ ባሕላችን የወለደው ችግር ነው ብሏል። ይህን ችግር በመሠረታዊነት ለመቅረፍ እና በሀገራዊ ጉዳዮችና በብሔራዊ አጀንዳዎች ዙርያ የሚታዩ ልዩነቶችንና መካረሮችን ለማረቅ ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
መንግሥት አዎንታዊ የሰላም ባሕል እንዲሰፍን እና የሠለጠነ የፖለቲካ ባሕል ተገንብቶ ኢትየጵያውያን ችግሮቻቸውን በጠረጴዛ ዙርያ በሃሳብ አውድ ብቻ መፍታት አለባቸው የሚል ፅኑ እምነት አለው ነው ያለው፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብሏል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉ አካታች የኾነ ሃገራዊ ምክክር ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያገኘነው የማይተካ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል ለሁሉም አካላት የተከፈተ የትኛውንም ወገን የማይለይ አካታች የምክክር ዕድል ነው፡፡ በዚህ እድል ለመጠቀም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ዝግጁ ልንኾን ይገባል ነው ያለው።
ይህ ዕድል የኖረውን የወንድማማችነት ዕሴት ያዳከመውን የተበላሸ የፖለቲካ ባሕላችንን ከማከም ባለፈ ዘላቂ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የምክክር ዕድሉ በመሠረታዊ ጉዳዮቻችን ዙርያ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠር ፣እየዳበረ የሚሄድ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት፣ በመሃከላችን የእርስ በእርስ መተማመንን በመፍጠር የሕዝብን መተባበር እና አንድነት በማረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብሏል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጦርነትና አብዮት የተሟላ መፍትሔ የማያመጡ መኾናቸውን በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ የመጣ አሸናፊነት ጊዜያዊና መልሶ ቁርሾና ቂምን የሚያሳድር መንገድ መኾኑን ተምረንበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በውይይትና በምክክር ችግሮቻቸውን አለመግባባቶቻቸውን የመፍታት ድንቅ ባሕል የነበራቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን ይህ እሴት እየጎለበተ በመጣው ኋላቀር የፖለቲካ ባሕል ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ በመደብዘዝ ከፋፋይ ነጠላ ትርክት መገለጫችን እስከመኾን ደርሷል ነው ያለው።
በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት ከከረረ ልዩነትና ከግጭት ድባብ ለመውጣት ሀገራዊ ምክክር እንደመፍትሔ መጠቀማቸውን አንስቷል። እኛም ኢትዮጵያውያን ይህንን ማድረግ የማይሳነን ሕዝቦች ለመኾናችን በየአካባቢው ያሉ ባሕላዊ ዕሴቶቻችን ማሳያ ናቸው ብሏል።
ዘላቂ የኾነ መፍትሔን ለማምጣት በእውነተኛ ፖለቲካዊ መሻት በቅንነት ለውይይት ለሰጥቶ መቀበልና ለጋራ መፍትሔ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳት ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያውያን የመጣንበት የግጭትና የጦርነት አዙሪት በቃን የምንልበት ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው ብሏል። ግጭት ማንንም አሸናፊ የማያደርግ የጥፋት አዙሪት ስለኾነ የሀገራዊ ምክክር ሂደትን ስኬታማ ማድረግ ፣ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት፣ የሕግ የበላይነትን ማስፈን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትሆን ሀገር ለመገንባትና ሁላችንንም የጋራ አሸናፊ ለማድረግ ያግዘናል፡፡
ሁሉም አካል በምክክሩ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጽሑፍ እያቀረቡ ነው።
Next article“ምሁር በስሜታዊነት የሚነዳ ሰው አይደለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)