ለዓመታት የዘለቀው የባሕር ዳር- ዘጌ የአስፋልት መንገድ ጥያቄ!

7
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር- ዘጌ መንገድ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎት ይሰጣል፤ የጎብኝዎችን እንቅስቃሴ ያቀላጥፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የመንገድ ፕሮጀክት በ2010 ዓ.ም ነበር በ555 ሚሊዮን ብር በጀት ሥራ የጀመረው።
በሁለት ዓመት ከስድስት ወር ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ይህ 21 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር መንገድ ከተጀመረ ከሰባት ዓመት በላይ ቢቆጠርም እስካሁን አልተጠናቀቀም። ይህን ተከትሎም በጀቱ በተለያዩ ጊዜያት ማሻሻያ ተደርጎበታል።
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ያነጋገራቸው የዘጌ ከተማ ነዋሪ አንተሁን ምስክር የባሕር ዳር- ዘጌ መንገድ በተቀመጠለት ጊዜ አለመጠናቀቁ ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተቸግረናል፤ ማኅበረሰቡ ከተሽከርካሪ ወርዶ ተሽከርካሪዎችን እየገፋ የሚያሳልፍበት ሁኔታም አለ ብለዋል።
በመንገዱ አለመስተካከል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች መንገድ ትራንስፖርት ያወጣውን ትክክለኛው ታሪፍ ተጠቅመው እያገለገሉ አለመኾኑንም አንስተዋል።
መንገዱ በተቀላጠፈ ሁኔታ ተጠናቆ የአካባቢው ማኅበረሰብ እፎይታ እንዲያገኝ ቢደረግ ሲሉም ጠይቀዋል።
ሌላኛው የመሐል ዘጌ ነዋሪ ተስፋ ሺህመካው የመንገድ ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ አለመጠናቀቁ የዘጌ እና አካባቢው አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን ምርቶች በተቀላጠፈ ሁኔታ ለገበያ ለማቅረብ አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግረዋል።
የጸጥታ ችግሩ ለመንገዱ መጓተት እንደ ዋና ምክንያት ሊወሰድ አይገባምም ብለዋል። ዘጌ እና አካባቢው የክልሉ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ቢኾንም ከሰባት ዓመት ወዲህ ቱሪስቶች የውኃ ትራንስፖርት ብቻ ጠብቀው ለመጠቀም የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ይህ ደግሞ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ እና በቱሪዝም ዘርፋ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ መንገዱ በፍጥነት ሊሠራልን ይገባል ብለዋል።
የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (cccc) የባሕር ዳር-ዘጌ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሊዮ ቼን ቢን ሊ ከጸጥታ ችግሩ ባሻገር የወሰን ማስከበር ተግባራት መጓተት፣ የሥራ ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ፣ የአፈር ማፈሻ እና የጠጠር ማምረቻ ማስፋፊያ ቦታ አለመፈቀድ መንገዱ በተቀመጠለት የማጠናቀቂያ ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ማድረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ግን አንዱ የጠጠር ማፈሻ ቦታ ስለተፈቀደ ለሙሌት የሚኾን ጠጠር የማጓጓዝ ሥራ ጀምረናል ነው ያሉት። ተጨማሪ ማሺነሪዎች የማስገባት ሁኔታ መኖሩንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር ፕሮጀክት አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ የባሕር ዳር – ዘጌ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት መጀመሪያ ላይ የነበረው ሥራ ተቋራጭ ለአምስት ዓመት ያክል ሲሠራ ቢቆይም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ስለነበር ውሉ ተቋርጦ ለቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሥራ ተቋራጭ መሠጠቱን ተናግረዋል።
ተቋራጩ በአንድ ዓመት ጊዜ ሠርቶ በማጠናቀቅ በ2016 ዓ.ም እንዲያስረክብ ውል ተይዞ እንደነበርም አስታውሰዋል። ኾኖም ግን በ2015 መጨረሻ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሲያጓትተው ቆይቶ አሁንም መጨረስ አልተቻለም ነው ያሉት።
በቅርቡ ውይይት ተደርጎ የሥራ እንቅስቃሴ መጀመሩንም የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም ከክልሉ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን እና ችግሮችን እየፈታን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንሠራለን ብለዋል።
አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ 64 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱንም ጠቅሰዋል።
ከባሕርዳር- ዘጌ መገንጠያ ድረስ ያለውን 10 ኪሎ ሜትር መንገድ በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በኅዳር እና ታኅሣሥ ወር 2018 ዓ.ም የከወኗቸው ቁልፍ ተግባራት።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናታዊ ጽሑፍ እያቀረቡ ነው።