
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ክልል ምክር ቤት አዳራሽ የ2012 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አስናቁ ደረስ የክረምቱ የበጎ ፍቃድ ሥራ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና የሴቶችና ሕጻናት ጥቃት መከላከል ላይ ዋና ትኩረቱን እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ደረጃ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) ደግሞ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰው የመሆን ትርጉም በተግባር የሚታይበት እንደሆነ አስረድተዋል። ይህም ከራስ በላይ ለሌሎች በመኖር የበጎ ፈቃድ ተግባር እንደሚገለጽ አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ደግሞ ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ሌሎች ችግሮችን በጋራ መጋፈጥ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። ‘‘በበጎ ፍቃድ ትንሽ ብንሠራም በጎ ነው’’ ሲሉም ወጣቶች በሚችሉት መጠን ለበጎ አድራጎት ተግባር እንዲተጉ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ወጣቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአማራ ክልል ወጣቶች ፌደሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡