
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ገብተዋል።
በወረዳው ጣሊያን፣ ወይበይኝ፣ ብር አዳማ እና አጎራባች ቀጣናዎች ላይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች መገዳደል ለቋሪት እና አካባቢው ሕዝብ ያስገኘው ትርፍ እንደሌለ በመረዳት የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ገልጿል።
ባልተገባ መንገድ ወደ ጫካ ገብተን የራሳችንን ማኅበረሰብ የከፋ ችግር ላይ በመጣላችን ተጸጽተናል ነው ያሉት።
በጦርነት የሚፈታ ችግር የለም፤ አሁንም ተደናግረው ጫካ ያሉ ጓደኞቻችን ከዚህ በኃላ መገዳደል በቃን ብለው የሰላምን መንገድ ተከትለው መግባት አለባቸው ብለዋል።
የቋሪት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መኳንት ወርቅነህ ታጣቂዎቹ በተሳሳተ መንገድ ተደናግረው ወደ ጫካ ገብተው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ቆም ብለው አስበው የሰላምን መንገድ መከተላቸው የሚደነቅ መኾኑን አንስተዋል።
ከምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሌሎች ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም ወደ ሰላም መጠው መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
