
ወልድያ: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከተማዋን በኮሪደር ልማት እያስዋበ ነው።
የኮሪደር ልማቱም ማኅበራዊ ፋይዳው ጉልህ መኾኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት ወጣቶች እና አዛውንቶች በአካባቢያቸው የሚያርፉበት የተመቻቸ ነገር አልነበራቸውም። አሁን ላይ ግን የኮሪደር ልማቱ የደከመ አዕምሮን ማሳረፊያ፣ መንፈስን ማደሻ፣ ለአዛውንቶች ትላንትን እያስታወሱ ለመጫወት የሚያስችል ማረፊያ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
ይህ ልማት ቀደም ብሎ ሊሠራ ይገባው ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ በችግር ውስጥ ኾኖ አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ መሠራቱ የከተማዋን ራሷን የማልማት አቅሟን ያሳያል ነው ያሉት።
ልማቱ የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ ቀይሯል ብለዋል። እንዳይበላሽ መጠበቅ እና የዘመነች ከተማን ለትውልድ ማሻገር እንደሚገባም አንስተዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ሙሐመድ ሷሊህ የኮሪደር ልማቱ ሊያሟላው የሚገባውን መስፈርት ጠብቆ መሠራቱን ገልጸዋል።
ልማቱ በከተማ አሥተዳደሩ መሀንዲሶች እና ባለሙያዎች ዲዛይን መደረጉ እና በራስ አቅም መሠራቱ የይቻላል መንፈስ እንዲጎለብት ማድረጉን ተናግረዋል።
ወደፊት ከፍ ያሉ ኘሮጀክቶችን የመፈፀም አቅምም መዳበሩንም ገልጸዋል። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ 2 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ተሠርቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ተጨማሪ 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር በ2 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
ከጉቦ በር አስከ ጅቡቲ መውጫ ካለው የአስፋልት ንጣፍ ጎን ለጎን እየተሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከጎንደር በር ሸሁ አደባባይ እስከ ዩኒቨርሲቲው ድረስ ያለው በሙሉ አቅም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከፒያሳ አውራ ጎዳና ጀነቶበር ያለው የአምስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት የካቲት ወር ላይ ለመጀመር መታቀዱን እና በ2018 በጀት ዓመት የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች የኮሪደር ልማት ሙሉ በሙሉ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማት ሥልጡን ከተማ እና ሥልጡን ማኅበረሰብ መገንባት የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል። የከተማዋን ሕዝብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማት የተነሱ ወገኖችን የማደራጀት ሥራ አየተሠራም ነው። ከ250 በላይ የመስሪያ ቦታም ጎንደር በር፣ አዳጎ፣ መልካቆሌ እና ሆስፒታል አካባቢዎች እየተገነባ ነው ብለዋል።
የመስሪያ ቦታዎቹ ሲጠናቀቁ በልማት የተነሱ ወጣቶች በክላስተር ተደራጅተው እንዲረከቡ እና ወደ ንግድ ሥራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ነው ያሉት።
እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት የኅብረተሰቡን አብሮነት ያጎለበተ፣ የታዳጊዎች እና የአዋቂዎችን መንፈስ ለማደስ አቅም የፈጠረ መኾኑንም ገልጸዋል።
የከተማዋ የመልማት አቅም እና ፀጋዎቿ ሰፊ በመኾናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እና ተወላጆች በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው እና በጉልበታቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ፤ የሠለጠነች ከተማን ለትውልድ ለማሻገር እንዲተባበረሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
