
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ 230 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው የኤሌክትሪክ ሳብስቴሽን ግንባታ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ የከተማዋ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መኾኑ ተገልጿል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ የተገነባው 230 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው የኤሌክትሪክ ሳብስቴሽን ፕሮጀክት በ2015 ዓ.ም በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጭ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ፕሮጀክቱ በ10 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲኾን እስከ 130 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ያሉ ከተሞችን ማዳረስ የሚችል ነው።
ከዚህ በፊት የከተማዋ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በሞባይል ሳብስቴሽን የሚሰጥ በመኾኑ ተደጋጋሚ የኀይል መቆራረጥ ይኖር እንደነበር ተገልጿል።
ይህም በከተማዋ የሚገኙ ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ምርት እንዳያመርቱ እና ተጨማሪ ወጭ እንዲያስከትል ማድረጉ ነው የተብራራው።
በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኘው የውከ ሶንግ ማኑፋክቸሪንግ የፕላይ ውድ ፋብሪካ አስተባባሪ አበበ ተስፋዬ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት የኀይል እጥረት በመኖሩ ፋብሪካው ሙሉ አቅሙን መጠቀም አልቻለም።
ይህም ጄኔሬተሮችን በመጠቀም ለተጨማሪ ወጭ እንዲዳረጉ አስገድዷቸው ነበር።
አሁን ግን ሳብስቴሽኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ የኀይል መቆራረጥ ሳይኖር ቀን እና ሌሊት በመሥራት ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም መቻላቸውን ገልጸዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አስራት መሰለ በበኩላቸው የኀይል አቅርቦት ችግር በከተማዋ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ መሰናክል እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ግን ችግሩ ተፈትቶ ነባር እና አዲስ ባለሃብቶች የማምረት አቅማቸውን እያሳደጉ መኾኑን ተናግረዋል።
ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ማሽኖችን ይዘው የሚመጡ ባለሃብቶች ፍላጎት መጨመሩንም ጠቁመዋል።
የከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አወቀ ስሌ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በነበሩ የጸጥታ ችግሮች የተፈተነ ቢኾንም በሚመለከታቸው አካላት ጥረት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የኅብረተሰቡን የመብራት ችግር ከመፍታት በተጨማሪ ለከተማዋ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘላቂ መፍትሄ መስጠቱንም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
