የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ጥበቃ ላይ ነው፡፡

754

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ ውል ሰጥቶ ሥራ ለማስጀመር ከገንዘብ ሚኒስቴር ገንዘብ እንዲለቀቅለት ጠይቆ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገነባው የአዋሽ ኮምልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለሥራው ፈተና ሆኖበታል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አብዱልከሪም መሐመድ (ኢንጂነር) ለአብመድ እንደተናሩት ፕሮጀክቱ ከአዋሽ-ኮምቦልቻ እና ከኮምቦልቻ- ሀራ ገበያ በሚል በሁለት ምዕራፍ የሚሠራ ነው፡፡ ከአዋሽ-ኮምቦልቻ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራው 99 በመቶ ተጠናቅቆ የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

”የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለ12 ወራት የሚቆይ የኃይል ዝርጋታ ኮንትራት እንዲፈጸመ አሳውቆናል፡፡ እኛም ከ12 ወራት በኋላ ለፕሮጀክቱ ኃይል ይቀርባል ብለን እየተጠባበቅን ነው“ ብለዋል ኢንጂነር አብዱልከሪም፡፡

የአዋሽ ኮምቦልቻ ባቡር ፕሮጀክት ከዓመታት በፊት ኃይል ይፈልግ እንደነበርና የኃይል አቅርቦቱ እንደዘገዬም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በተባለለት ጊዜ ሥራ አለመጀመሩ ሀገሪቱን ብዙ ነገር እያሳጣት እንደሆነም ኢንጂነር አብዱልከሪም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሠርቶ ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ “ሥራው እንዳለቀ የስድስት ወር ሙከራ ተደርጎ ከተቋራጩ የመረከብ ሥራ ይሠራ ነበር” ያሉት ኢንጂነሩ የኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ መረከብ እንዳልተቻለም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ባለድርሻ አካላት በተመጋገዝ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ እንደሚገባቸው ጠይቀዋል፡፡

አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 92 በመቶ የደረሰው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክትን የቱርኩ ያፒ መርኪዚ ነው እየሠራው የሚገኘው፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የባቡር ፕሮጀክቱ ኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት ኃላፊ ደስታዓለም ኃይሉ የኃይል አቀርቦቱን በአንድ ዓመት ለመጨረስ ውል መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ የኃይል ማስተላለፊያና የኃይል ማከፋፋያ ጣብያ ውሎች እንደተፈረሙም አስታውቀዋል፡፡ የቅደመ ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በውሉ መሠረት ሙሉ በሙሉ ሥራ ለመጀመር ቅድመ ክፍያ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ቅድመ ክፍያ እንዲከፈልም ገንዘቡ እንዲገባላቸው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ደብዳቤ እየተጻጻፉ መሆናቸውንና በቅርቡም ውይይት እንደሚኖራቸው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ሥራውን ለመጀመር ገንዘብ ሚኒስቴር ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ እንደሚወስነውና ገንዘቡ እንደተፈቀደ ሥራውን ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አብመድ በዚህ ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦት ችግሮች ዙሪያ ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ከዚህ ቀደምም መሥራቱ የሚታወስ ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
Next articleየኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና ሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል የክረምት ወቅት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዋነኛ ትኩረት እንደሆኑ የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።