ቦይንግ ታማኝነቱ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

213
ቦይንግ ታማኝነቱ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፕላን መከስከስን ተከትሎ ቦይንግ ውጥረት ውስጥ ገብቷል፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 06/2011ዓ.ም (አብመድ) ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ሞዴሎችን ከበረራ ያገዱ ሀገራት ቁጥር ከ50 በላይ ደርሷል፡፡

በተለያዩ አየር መንገዶች የታዘዙ ከ4ሺህ በላይ ቦይንግ አውሮፕላኖችም ተሰርዘዋል፡፡ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ሞዴሎችን ከበረራ ያገዱ ሀገራት ቁጥር ከ50 በላይ ደርሷል፡፡

አሜሪካ ‹‹አውሮፕላኑ ለይ ችግር አላገኘሁበትም፤ ከበረራ የማግድበት ምንም ምክንያትም የለም›› ስትል ቆይታለች፡፡ የኋላ ኋላ የአሜሪካ የመንገደኞች በረራ አገልግሎት አደጋው ከደረሰበት ስፍራ እና ከሳተላይት በሰበሰብኩት መረጃ መሰረት በኢንዶኔዥያ ከአምስት ወራት በፊት በተከሰከሰው እና የ189 ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው አደጋ እና ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ በደረሰው አደጋ መካከል መመሳሰል አግኝቸባቸዋለሁ ብሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ቦይንግ አውሮፕላኖቻቸው እንዳይበሩ አግደዋል፡፡
የዓለማችን ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ከአውሮፓዊያን 1990ዎቹ ወዲህ ገበያውን ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡

ቦይንግ በአሜሪካ ፖለቲካ ድጋፍ በማድረግ እና በሌሎች ዋና ዋና እንቅስቃሴዎች ላይም ተፅዕኖ የሚያሳድር እና ጉልህ ሚና የሚጫወት ኩባንያ ነው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመውን የአውሮፕላን አደጋ ተከትሎ በገበያው ላይ ያለው የድርሻ መጠን በእጅጉ እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ይህም ከ9/11 የሽብር ጥቃት በኋላ የመጀመርያው ነው ተብሏል፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ አየር መንገዶች የታዘዙ ከ4ሺህ በላይ ቦይንግ አውሮፕላኖችም ተሰርዘዋል፡፡

አሜሪካ ቦይንግ አውሮፕላኖቿ እንዳይበሩ ማገዷ ኩባንያው በሀገሪቱ ያለውን ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚቀንስም ሊሆን ይችላል፡፡
ይሁንና የአደጋው ትክክለኛ መንስዔ ተጣርቶ እስኪታወቅ በኩባንያው ሙሉ በሙሉ መፍረድ አይቻልም ብሏል ሲጂቲኤን በዘገባው፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleናሳ ቀልድ አዋቂ ግለሰቦችን በጠፈርተኛነት ሊቀጥር ነው፡፡
Next article‹‹ደስ ስላላችሁ ደስ ብሎኛል!›› አና ጎሜዝ-ለኢትዮጵያዊያን