የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በማጎልበት በአመለካከት እና በክህሎት ብቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

10
ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር የቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከመደበኛው ትምህርት ውጭ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል።
ተማሪ ራኒሃ ሙሐመድ እና ማሪቱ ነጋ የቁጥር ሁለት አደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ተጨማሪ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተመድቦላቸው መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጧቸው መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ ሴት ተማሪዎች በልዩ ጥናት እንደሚሳተፉ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚማሩ እና በክበባት እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
ታዲያ የማንበብ እና የትምህርት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱንም አስረድተዋል።
በዚህም በመምህራን በኩል በቂ እገዛ ስለተደረገላቸው በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ማምጣታቸውንም ነግረውናል።
ሴት ተማሪዎችን በትምህርታቸው ብቁ ለማድረግ የመምህራን ጥረት ከፍተኛ መኾኑን የአማርኛ ቋንቋ መምህርት አጥቢያነሽ አስናቀው ገልጸው ተማሪዎች በሚደረግላቸው እገዛ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ተናግረዋል።
የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከመደበኛው ትምህርት ውጭ ለሴቶች ብቻ የማጠናከሪያ ትምህርት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ተምረው ያለፉትን ርዕስ በመከለስ፣ ወርክ ሽቶችን እና የተለያዩ ዘመናት ፈተናዎችን በመሥራት ሴት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በየነ አዳነ እንደሚሉት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በማጎልበት በአመለካከት እና በክህሎት ብቁ እንዲኾኑ እየተደረገ መኾኑን አብራርተዋል።
አጋዥ መጽሐፍትን ቤተ መጽሐፍት በማስገባት ተማሪዎች እንዲያነቡ እና እንዲረዳዱ እየተደረገ ነው ብለዋል። በትምህርት ቤቱ ለሴት ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረግላቸዋልም ነው ያሉት።
ተማሪዎች ተሰጧቸውን እንዲያሳድጉ በክበባት ተሳታፊ በመኾን አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እየተደረገ ነው ያሉት ኀላፊው የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ሴት ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲጎብዙ ሁሉም ወላጅ ድጋፍ በማድረግ ኀላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ኀላፊው መልዕክት አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደሳለኝ አያና እንደ ዞን የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ በልዩ ጥናት እና በቲቶሪያል በመደገፍ በተለያዩ አደረጃጀት ዘርፎች ሴቶችን ለማብቃት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ብቃት ባላቸው እና በተመረጡ መምህራን ትምህርታቸውን እንዲማሩ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስረድተዋል።
በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ ለሚሰጠው ፈተና ሴቶች ከወንዶች ዕኩል ውጤት እንዲያስመዘግቡ በተለያዩ ተግባራት የሥነ ልቦና ትምህርቶች እና የምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው መኾኑንም አብራርተዋል።
የተሻለ ውጤት ለሚያመጡ ሴት ተማሪዎችም የማበረታቻ ሽልማት እና ዕውቅና ይሰጣልም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተደረገ ነው።
Next articleፋይዳ መታወቂያ ለሴቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል።