“ትሕትና እና ፍቅር ለክርስቲያኖች ከፈጣሪ የተሰጠ መመሪያ ነው” ቆሞስ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ

17
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በላሊበላ ከተማ በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ላይ ከሚከወኑ መርሐ ግብሮች ውስጥ የእንግዶች እግር እጥበት አንዱ ነው። የእግር እጥበት መርሐ ግብሩ በዋናነት እንግዶች ወደ ከተማዋ ከገቡ ጀምሮ እስከ በዓሉ ዋዜማ ይከናወናል።
በዚህ ዓመትም የከተማዋ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን እግር በማጠብ እየተቀበሉ ይገኛሉ።
አቀባበል ከተደረገላቸው እንግዶች መካከል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን በለሳ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት ክንዴ አበበ አንዱ ናቸው። አቶ ክንዴ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምረው በላሊበላ እያከበሩ እንደኖሩ ነግረውናል። በዚህ ዓመትም ከሰባት ቀን የእግር ጉዞ በኋላ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ላሊበላ ከተማ ተገኝተዋል።
በቀጣይ ቀናት የቅዱስ ላሊበላት የጥበብ እጆች ያረፈባቸውን ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በመጎብኘት እና ሌሎች ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን በማከናዎን፣ በዕለቱ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን እና የቅዱስ ላሊበላን የልደት በዓል ተካፍለው እንደሚመለሱ ነግረውናል። በዓሉን ለማክበር ለሚጓዘው ምዕመን በየቦታው የሚደረገው እንክብካቤ የማኅበረሰቡን የቆየ የመከባበር ባሕል ያሳየ እና ለቀጣዩ ትውልድ ትምህርት ሰጭ መኾኑን አንስተዋል።
የልደት እና የጥምቀት በዓል ዝግጅት የወጣቶች አሥተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አበበ ሰጣርጌ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ለማክበር ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን እግር ማጠብ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያቱን እግር አጥቦ ትሕትናን እና መከባበርን ያሳየበትን መንገድ ለመከተል ያለመ ነው ብለዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚታየው መከባበር እና መረዳዳት በማንኛውም ጊዜ እንዲጠናከር እንደሚሠሩም ነው የገለጹት።
የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ ቆሞስ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ የእግር እጥበት ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠብ ለሃይማኖቱ ተከታዮች ትሕትናን እና ፍቅርን ያስተማረበት ሥርዓት ነው ብለዋል። “ሥርዓቱ ለክርስቲያኖች ሁሉ መለኮታዊ መመሪያ እንደኾነም” አንስተዋል።
አባቶችም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የእንግዶችን እግር በማጠብ ፍቅርን አሳይተዋል ብለዋል። አሁን ላይም በበዓሉ ለመሳተፍ ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን እግር የማጠብ፣ ቦታ የማሳየት፣ የመንከባከብ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የቀጣዩ ትውልድም ሥርዓቱን ማስቀጠል ይገባዋል ነው ያሉት።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጄ እንግዳ መቀበል የላሊበላ ከተማ ሕዝብ መገለጫ መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ለመታደም ወደ አካባቢው የሚመጡ እንግዶችን እግር ማጠብ የማኅበረሰቡ እሴት መኾኑን ነው የተናገሩት። ወጣቶች ይህንን መልካም እሴት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወጣቶችን ያላሳተፈ የሰላም ግንባታ ሥራ አይሳካም።
Next articleደሴ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የልማቱ ተቋዳሽ እየኾነች መጥታለች።