ወንጀለኞችን ማጋለጥ ለጋራ ሰላም መፍትሔ ነው።

1

ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ያለመ የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከ4 ሺህ 500 በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ የተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል እሸቴ ናቸው።

በከተማው የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎች በሚፈጽሙት ወንጀል ምክንያት በሰዎች ላይ የሕይዎት መጥፋት፣ የአፈና፣ የስርቆት እና የአካል ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይህንን ለመከላከል አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ንብረታቸውን ሕጋዊ ውል በመስጠት ወንጀለኞችን በማጋለጥ እና በመጠቆም ኀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

እስከ ጦር መሣሪያ መጫን እና ማዘዋወር ድረስ በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ እየተፈጸመ መኾኑን የገለጹት ደግሞ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል አደራጀው ሰረበ ናቸው።

በሚፈጸሙ ወንጀሎች የሰዎች ሕይዎት በከንቱ እየጠፋ በመኾኑ ወንጀል እና ወንጀለኞችን ማጋለጥ ይገባል ብለዋል። “ወንጀለኞችን ማጋለጥ ለጋራ ሰላም ሲባል እንደኾነም ነው” የተናገሩት።

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ደጀኔ ልመንህ በባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ አማካኝነት የሚፈጸሙ ወንጀለኞችን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ኀላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የከተማዋን አስተማማኝ ሰላም እና ጸጥታ ለማጽናት በሚሠራው ተግባር የሁሉም ወገን የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የደብረ ብርሃን ከተማ ሰላሟ የተጠበቀ ከኾነ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው የሰዓት ገደብ እንደሚነሳም ጠቁመዋል።

በጥቂት አሽከርካሪዎች የሚፈጸሙ ወንጀሎች የከተማዋን ገጽታ እያበላሸ በመኾኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ሲያሳልጡ የኖሩ እሴቶች ናቸው።
Next articleወጣቶችን ያላሳተፈ የሰላም ግንባታ ሥራ አይሳካም።