
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን አንጎት ወረዳ በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።
የሰላም አማራጭ የተቀበሉትን ታጣቂዎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ታጣቂዎቹ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ እናስመልሳለን በሚል አስተሳሰብ ጫካ በመግባት በሕዝባቸው ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት ሲያደርሱ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
አሁን ላይ የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ እና ለማገልገል የሰላም ጥሪውን መቀበላቸውን ገልጸዋል። የአንጎት ወረዳ ምክትል ዋና አሥተዳዳሪ ካሳነው አዲስ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በብጥብጥ እና በጦርነት ሳይኾን በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ልጆቹን መክሮ እንዲያስገባ በተለያዩ መድረኮች የግንዛቤ ፈጠራ መሠራቱን ገልጸዋል። የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላም ወደ ሕዝብ የመጡ ወጣቶችን ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የወረዳው አሥተዳደር ምክር ቤት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል አዛዥ የግጭቶች ሁሉ መፍቻ መንገድ ሰላማዊ ውይይት እንጅ ነፍጥ አንግቦ ጫካ በመግባት ሕዝብን መጉዳት አይደለም ብለዋል።
ሁሉም ነገር የሚገኘው ከሰላም በመኾኑ ሌሎች ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
