‎እምቦጭ አሁንም የጣና ሐይቅ ሥጋት

21

‎ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የእምቦጭ አረም በፍጥነት የመስፋፋት ባሕሪ ያለው ማንኛውንም የውኃማ አካል የሚያጠቃ አረም ነው፡፡ አረሙ አጭር ጊዜ ራሱን የማስፋፋት አቅም ያለው እና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታን የሚቋቋም በመኾኑ በውኃ አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡

‎አረሙ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው በ2004 ዓ.ም ስለመኾኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አረሙን ለማስወገድ በተለያዩ አካላት ርብርብ ቢደረግም እስካሁን ከሐይቁ ማጥፋት አልተቻለም፡ከጥቅምት እስከ ታኅሣሥ ያለው ወቅት አረሙ አብቦ ፍሬ የሚያፈራበት በመኾኑ አረሙን ከሐይቁ ላይ የማስወገድ ሥራው ምን ይመስላል?

‎የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዳኛው እጅጉ የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ከተከሰተ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ብለዋል፡፡ አረሙን ለማስወገድ በሰው ጉልበት እየተሠራ ቢኾንም መጥፋት ግን አልቻለም ነው ያሉት፡፡

‎ከዚህ በፊት አርሶ አደሮች በጉልበታቸው እምቦጭ ሲያስወግዱ የተለያዩ አልባሳት እና ሰውነታቸው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የንጽህና መጠበቂያ ይቀርብ እንደነበር አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ ግን ይህ አቅርቦት እንደሌለ ነው የገለጹት፡፡

‎አረሙ አሁን የሚያብብበት ወቅት በመኾኑ ስር ሳይዝ አረሙን ለማስወገድ በሳምንት ሁለት ጊዜ ማኅበረሰቡ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

‎የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ የአካባቢ ጥበቃና ሥነ ምኅዳር ተፋሰስ አያያዝ ቡድን መሪ መሰለ ተባባል እምቦጭን ለማጥፋት ለተከታታይ ዓመታት የተለያዩ ሥራዎች ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በጸጥታው ችግር ምክንያት መቀዛቀዙን አንስተው አሁን ላይ ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

‎አረሙ በተከታታይ ሢሠራ እየቀነሰ ነበር ያሉት ቡድን መሪው አሁን ላይ መጨመር አሳይቷል ብለዋል፡፡ አረሙ በዘር እና በግንድ የሚራባ በመኾኑ መታረም ያለበት በውኃ ላይ እንደተንሳፈፈ ነው፤ ይህም  በትንሽ ጉልበት ብዙ አረም ለማስወገድ ያግዛል ነው ያሉት፡፡ በወረዳው በዚህ ዓመት ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ ካለው 958 ሄክታር ውስጥ 202 ሄክታር የማስወገድ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

‎በክልል ደረጃ አረሙን ለማስወገድ አጋር አካላትን አቀናጅቶ ከመሥራት እና ድጋፍ ማድረግ ላይ ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

‎ችግሩ አሳሳቢ በመኾኑ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እና ሙከራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ለአብነትም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጣና ብዝኀ ሕይወትን መጠበቅ ላይ የሚሠራው የደንገል ፕሮጀክት አስተባባሪ ንብረት አስራደ (ዶ.ር) የደንገል ተክልን (ፓፒረስ) በሐይቁ ዳርቻዎች እንደሚተክሉ ተናግረዋል፡፡ በብዙ የሐይቁ ቦታዎች ደንገል ባለበት እምቦጭ እንዳይስፋፋ ማድረጉ በተግባር የታየበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

‎በጣና ሐይቅ እና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ እና የእምቦጭ አረም ማስወገድ አስተባበሪ ጤናው ምንውየለት የእምቦጭ አረም በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሄክታር የሚደርሰው የሐይቁ ክፍል በአረሙ ተሸፍኗል ብለዋል፡፡

‎ከዚህ ውስጥ ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 800 ሄክታር የሚኾነው አረም ቢወገድም፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት ማኅበረሰቡን በስፋት አነቃንቆ ለመሥራት አልተቻለም ነው ያሉት፡፡

‎የእምቦጭ አረም ከዚህ ቀደም ከነበረበት የምስራቅ ጣና አካባቢ በተጨማሪ አሁን ላይ በሰሜን ጎጃም እና በባሕር ዳር ዙሪያ እየተስፋፋ ይገኛል ብለዋል፡፡

አረሙ ሙሉ በሙሉ እስካልተወገደ ድረስ ሲነቀል በእጥፍ የመባዛት ባሕሪ ስላለው ሰፊ ሥራን እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

‎በዩኒቨርሲቲዎች እምቦጭ ላይ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ቢኖሩም ከሙከራ ያለፈ አይደለም ነው ያሉት፡፡ የደንገል መትከል ሥራው እየተሠራበት ያለ ነው፤ እምቦጭ እንዳይስፋፋ ከማድረግ ባለፈ ሐይቁን ከብክለት የሚታደግ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

‎እንደ ክልል እምቦጭ የማስወገዱ ሥራ ከተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ጋር ተያይዞ እንዲሠራ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ለማኅበረሰቡ የሚደረጉ የአልባሳት እና የቁሳቁስ ድጋፎች የቆመው በበጀት ችግር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

‎አሁን ላይ ለእምቦጭ የተሠጠው ትኩረት ቀንሷል ያሉት አስተባባሪው የሚመለከታቸው ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው፤ ለዚህም እንቅስቃሴ ጀምረናል ነው ያሉት፡፡

‎ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው ማኅበረሰብ ሕይወት ከሐይቁ ጋር የተቆራኘ በመኾኑ ሐይቁን ከአረሙ መታደግ የህልውና ጉዳይ መኾኑን አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article4 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ መስጠቱን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።
Next articleሕዝብን ለመካስ እና ለማገልገል የሰላም አማራጭን ተቀብለናል።