4 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ቦታ መስጠቱን የደቡብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።

4
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) ማሪሁን አስማማው በነፋስ መውጫ ከተማ የምግብ ዘይት ለማምረት 4ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተቀብሏል፤ አሁን ላይ የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ ላይ መኾኑን ተናግሯል። በቅርቡም ግንባታ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
የዘይት መጭመቂያው ለ150 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራልም ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡የደጀን አለነ ነዳጅ ማደያ ሥራ አሥኪያጅ ፍቅር አስቻለ በበኩላቸው ድርጅታቸው በ2014 ዓ.ም ቦታ ተቀብሎ በ2016 ዓ.ም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ማደያው በአካባቢው የጸጥታ ችግር ቢያጋጥምም ችግሩን ተቋቁሞ በመሥራት ሕዝብ እያገለገለ መኾኑንም ተናግረዋል።
የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የሽዬ መንግሥት በከተማ አሥተዳደሩ 24 ባለሃብቶች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥም 18ቱ አምራች ናቸው። ሰባቱ ደግሞ ማምረት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
ከሦስተኛ ወገን ነጻ ኾኖ እና የመሠረተ ልማት ተሟልቶለት ባለሃብቶችን የሚጠብቅ መሬት መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ቦታ ከወሰዱ በኋላ ወደ ሥራ ለማይገቡ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ከድጋፍ በኋላም ሁለት ባለሃብቶች መሬታቸው መነጠቁን እና ለስምንት ባለሃብቶች ደግሞ በተለያዩ ደረጃዎች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ክንድየ መኬ በበጀት ዓመቱ ለ68 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና ቦታ መስጠታቸውን ገልጸዋል። የኢንቨስትመንት ቦታ የወሰዱት 65ቱ ባለሃብቶችም 4 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ ለ7ሺህ 500 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተናግረዋል፡፡ አብዛኞቹ ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች መሠረተ ልማት የተሟላላቸው እና ለልማት ምቹ እንደኾኑ ጠቅሰዋል፡፡
አልሚዎች እንዳይጉላሉ ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ልማትን ለማፋጠን ቁርጠኛ እንደኾኑም አንስተዋል፡፡ ወደ ልማት ያልገቡ ሦሥት ባለሃብቶች መሬትም መነጠቁን ገልጸዋል፡፡
የደብረታቦር ሰብስቴሽን ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ በመጀመሩ በዞኑ ለተሰማሩ አልሚዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት ኀላፊው ባለሃብቶች የሚፈልጉትን የኀይል መጠን ለማቅረብ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
ወደ ዞኑ ለሚመጡ አልሚዎችም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሁለቱም ተከራካሪዎች ወደው እና ፈቅደው የሚሄዱባቸው አማራጭ ሥርዓቶች ናቸው” አቶ ዓለምአንተ አግደው
Next article‎እምቦጭ አሁንም የጣና ሐይቅ ሥጋት