መንግሥት የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የገባውን ቃል እንዲፈጸሙላቸው የበየዳ ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ።

279

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ቢሮ የፕሮጀክቱ የአዋጭነት ጥናት እና ዲዛይን መጠናቀቁን ገልጾ በጀት እንደተገኘ ችግሩ እንደሚፈታ አስታውቋል።

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሰሜን ጎንደር ዞን የበየዳ ወረዳ ነዋሪዎች ከተከዜ የኃይል ማመንጫ ግድብ ከ50 ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ቢገኙም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ የወረዳው መዲና ድል ይብዛ ነዋሪዎች ‘‘መንግሥት በ2012 ዓ.ም ከተከዜ ኃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ ለማስገባት የገባውን ቃል ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባዋል’’ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከተማዋ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኗ በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፈባቸው እንደሚገኝ ነው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የገለጹት።

ሰሎሞን ተሻገር የሚተዳደረው የወንዶችን ፀጉር በማሳመር ነው። ወጣቱ እንደገለጸው የፀጉር ማሳመር ሥራ የሚሠራው ለከተማው በቀን 8 ሰዓት አገልግሎት በሚሰጠው የነዳጅ ጄነሬተር ኃይል በመጠቀም ነው። ቀሪ ጊዜውን ደግሞ የግሉን የነዳጅ ጀኔሬተር በመጠቀም ነው የሚሠራ። ለዚህም በወር ከ1 ሺህ 200 ብር በላይ ለነዳጅ ወጭ ያደርጋል። ከ125 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ስድስት አነስተኛ ጀኔሬተሮችም ለብልሽት ተዳርገውበታል።

ለከተማው በቀን ለ8 ሰዓታት ብቻ አገልግሎ በመስጠት ላይ የሚገኘው ጀኔሬተር በነዳጅ እና በተለያዩ ምክንያቶች ለሁለትና ሦስት ወራት አገልግሎት ሰጥቶ እስከ አንድ ወር እንደሚቆምም ነግሮናል። ለግላቸው ጀኔሬተር ነዳጅ የሚገዙት እስከ ደባርቅና ጎንደር እየተጓዙ መሆኑ ደግሞ የበለጠ አድካሚና ጊዜና ገንዘብ የሚጠይቅ እንደሆነባቸው ሰሎሞንና ሌሎች ነግረውናል፡፡

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሰሎሞን ብርሃን ደግሞ በብረታብት ብየዳ ሥራ ነው የሚተዳደረው። አቶ ሰሎሞንም ለከተማው አገልግሎት ከሚሰጠው የ8 ሰዓት የጀኔሬተር ኃይል በተጨማሪ የግሉን ጀኔሬተር በመጠቀም ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። በወር ከ6 ሺህ ብር በላይ ለነዳጅ ወጭ ያደርጋል። የተለያዩ የብረታብት ሥራ ውጤቶችንም ለማኅበረሰቡ እያቀረበ ይገኛል። ይህም ከ140 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ደባርቅ ተጉዘው ለብየዳ ሥራ የሚያወጡትን ወጭ አና ድካም ማስቀረቱን ነግሮናል። ለተወሰኑ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። የሠራተኛ ቁጥር በመጨመር የሥራ ዘርፎችን የማስፋት ዕቅድ ቢኖረውም ወረዳው የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኑ ዕቅዱን ማሳካት አለመቻሉን ነግሮናል።

ሁለቱን ነዋሪዎች አብመድ በአብነት ጠቀሰ እንጅ የወረዳው ነዋሪዎች የኃይል አቅርቦት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፤ ከወረዳው በጀት ከፍተኛ ድርሻ የጀኔሬተሮች ነዳጅ ይወስዳል፤ የጽሕፈት አገልግሎትና መሰል ሥራዎች ያለጀነሬተር አይታሰቡምና፡፡ እያንዳንዱ የሞባይል ተጠቃሚ አንድ ጊዜ ቻርጅ ለማድግ እስከ አምስት ብር ይከፍላል፤ በበየተዳ ከሞባይል የአየር ሰዓት ይልቅ የሞባይል ቻርጅ ውድ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ተማሪዎች በኩራዝ ነው የሚጠኑት፣ አንዳንዶች ደግሞ በቂ ብርሃን የማይሰጡ የሶላር መብራችን ይጠቀማሉ፡፡ ትምህርት በፕላዝማ ቴሌቪዥን የሚደገፈው ጀኔሬተሩ ነዳጅ ሲኖረው ብቻ ነው፡፡

የበየዳ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደገኝ ውባየሁ እንደነገሩን ከተከዜ ኃይል ማመንጫ ኤሌክትሪክ ለመሳብ ጥናት ተጠንቷል፤ ዲዛይንም ተሠርቷል። የሰብስቴሽን ቦታም በወረዳው ተዘጋጅቷል።

በ2012 በጀት ዓመት ሥራ እንደሚጀምር ቢገለጽም እስከዚህ ወቅት ድረስ የተጀመረ ነገር አለመኖሩን ኃላፊው ነግረውናል። ለዚህም የመንገድ ችግር እንደዋነኛ ምክንያት አንስተዋል። ከድልይብዛ ተከዜ 50 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ የገለጹት አቶ ታደገኝ ከድልይብዛ ልዋሬ 28 ኪሎ ሜትር መንገድ በክልሉ ገጠር መንገድ ቀደም ብሎ ተሠርቷል። ከልዋሬ እስከ ተከዜ ያለው ቀሪ 18 ኪሎ ሜትር መንገድ ዲዛይን ተሠርቶ ለመግንባት ግን ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ እንደሆነ በክልሉ ምላሽ መስጠቱን አስተዳዳሪው ነግረውናል። የኤሌክትሪክ ዝርጋታውን ለማከናወን የመንገድ ሥራ ግድ መሆኑንም ገልጸዋል። ችግሩ እንዲፈታ እስከ ፌዴራል ምንግሥት ድረስ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ውበት አቤ ‘‘የፕሮጀክቱ የአዋጭነት ጥናት ሲካሄድ ቆይቶ ከተከዜ የኃይል ማመንጫ እንዲሳብ ተወስኗል፤ ዲዛይኑም ተዘጋጅቷል። የዲዛይን ሥራ እና ጥናት ተጠናቀቀ ማለት ግን በቀጥታ ሥራ ይጀምራል ማለት አይደለም’’ ብለዋል። አቶ ውቤ እንዳሉት ዲዛይኑ እና ጥናቱ ቢጠናቀቅም የኃይል አቅርቦ ማስፋፊያ ቅድሚያ ማግኘት እንዳለባቸው ከተቀመጡት እንደምዕራብ ጎጃም ቡሬ እና አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ከተሞች ቀጥሎ በደረጃ ተቀምጧል። ለዝርጋታ የሚሆን በጀት እንደተገኘ ችግሩ የሚፈታ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከልዋሬ እስከ ተከዜ ያለው የ18 ኪሎ ሜትር መንገድ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው የከፋ ችግር እንደማይሆንም አመልክተዋል፤ ‘‘ዝርጋታው በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር (ታወር) የሚዘረጋ በመሆኑ የመንገድ መኖር አለመኖር የሚፈጥረው ተፅዕኖ ብዙም አለመሆኑን ገልጸዋል። በጀት መቼ ተገኝቶ የወረዳው ጥያቄ እንደሚመለስ ግን በእርግጠኝነት አልተናሩም፡፡

የበየዳ ወረዳ የኃይል ጥያቄ መመለስ የወረዳውን ነዋሪዎች የዘመናት ችግር ከመቅረፉም ባለፈ ሌላኛውን ኃይል የማያገኝ አጎራባች የጠለምት ወረዳም ከ40 ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት መስመር ዘርግቶ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዳባት ከፍተኛ ርቀት ኃይል ያኘውን የጃናሞራ ወረዳ የኃይል መቆራረጥ ለማስቀረትም በየዳ ቅርብ አማራጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleምጣኔ ሀብታዊ ትግል እና ኮሮናቫይረስ
Next articleሊቨርፑል ከ30 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡