የምግብ ዘይት ለዝቅተኛ ነዋሪዎች “የቅንጦት” ያህል እየኾነ ነው።

5
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ አሰለፈች በላይ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ስትኾን በመንገድ ዳር ጎመን እና ቆስጣ ዘርግታ በመሸጥ ነው የምትተዳደረው። ከዚህ ቦታ የምታገኛትን አስር፣ ሃያ ብር አጠራቅማ ሁለት ልጆቿን እንደምታሳድግ ነግራናለች።
ወይዘሮ አሰለፈች እንደምትለው ሁሌም የምትለፋው ለልጆቿ የዳቦ መግዣ እንዳታጣ ነው። ዘይት በቋሚነት መግዛት ከአቆምሁ ሁለት ዓመት አልፎኛል ነው ያለችው።
እንደ ወይዘሮ አሰለፈች ሁሉ ብዙዎች የዘይት ዋጋ በመናሩ ምክንያት ዘይትን በቀላሉ መግዛት ተቸግረዋል። ከዓመታት በፊት ሙሉ የወር አስቤዛ የሚገዛበት ገንዘብ በአሁኑ ወቅት አምስት ሊትር ዘይት ለመግዛት ተስኖታል።
በአንጻሩ ደግሞ በአማራ ክልል የሀገሪቱን የጥራት መስፈርት አሟልተው የምግብ ዘይትን ማምረት የሚችሉ 23 ግዙፍ እና መካከለኛ የዘይት ፋብሪካዎች ይገኛሉ።
በቢሊዮን ብሮች የተገነቡ እንደ ፊቤላ እና ደብልዩ ኤ ያሉ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች በቀን እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም አላቸው። እነዚህ ፋብሪካዎች እንኳን የአማራ ክልልን የሀገሪቱን የዘይት ፍላጎት መሙላት የሚችሉ ናቸው።
በግብርናው ዘርፍም ሲታይ የአማራ ክልል በቅባት እህሎች ምርት እና ምርታማነት ከሀገሪቱ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ክልሉ በ2018 የምርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት እህል ምርት ስለመመረቱ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ታዲያ የቅባት ምርት በስፋት እየተመረተ፣ የዘይት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በብዛት ተገንብተው ሳለ በክልሉ የዘይት ዋጋ መናር ከምን የመነጨ ይኾን? የሚለውን ጥያቄ ለዘርፉ ተዋንያን እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች አቅርበናል።
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው ዩኒሰን የምግብ ዘይት ፋብሪካ በቀን እስከ 50 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም ቢኖረውም በተጨባጭ እያመረተ ያለው ግን በወር ከ70 ሺህ ሊትር አይበልጥም ያሉት የፋብሪካው ምርትና ግብይት ኀላፊ ዘሪሁን ካሴ ናቸው።
የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው እንዳሉት በቡሬ ከተማ የሚገኘው ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካም ከማምረት አቅሙ 22 በመቶ ብቻ ነው እየተጠቀመ ያለው።
የኀይል አቅርቦት እጥረት፣ የግብዓት ዋጋ መናር፣ የባንክ ብድር ውስንነት እና የክልሉ የሰላም እጦት ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ እንዳደረጓቸው ኀላፊዎቹ አስረድተዋል።
ለአብነት ያነሳናቸው እና በክልሉ ያሉ ሌሎችም የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ከአለማምረት እስከ ማምረት ማቆም የደረሱ መኖራቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የአግሮፕሮሰሲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሳሁን ታዬ ነግረውናል።
የዘይት ፋብሪካዎች ተኪ ምርትን በጥራት እና በብዛት በማምረት የክልሉን የዘይት ፍላጎት መሙላት ቢኾንም እሳቤያቸው 90 በመቶ የሚኾነው የክልሉ የዘይት አቅርቦት ከውጭ የሚገባ መኾኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ አረጋግጠውልናል። ይህም በውጭ ምንዛሬ የሚገባ በኾኑ የዋጋ መናርን አስከትሏል ነው ያሉት።
አሁንም የመግዛት አቅም እንጂ የምግብ ዘይት አቅርቦት በገበያው ላይ እጥረት የለም ያሉት አቶ ፈንታው ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት እስካልጀመሩ ድረስ ችግሩ ሊቀጥል እንደሚችል ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ትልቁ ማነቆ የግብዓት ዋጋ መናር መሆኑን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የአግሮፕሮሰሲንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሳሁን ታዬ ያነሳሉ። 6 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረ አኩሪ አተር አሁን ላይ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል። ይህ በመኾኑ 5 ሊትር የምግብ ዘይት ከፋብሪካው ሲወጣ 1 ሺህ 500 ብር እንዲኾን አስገድዷል ነው ያሉት።
ግብዓት ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ቢኖርም ፋብሪካዎቹ የምግብ ዘይትን የሚሸጡበት ዋጋ የተጋነነ መኾኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ይገልጻል።
በገበያው ላይ የምግብ ዘይት ዋጋ ተለዋዋጭ ቢኾንም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ የ5 ሊትር ዘይት ዋጋ እስከ 1 ሺህ 950 ብር ደርሷል።
አሁንም መጭው የገና በዓልን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን የዘይት እጥረት ለማቃለል የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት በ1 ሺህ 550 ብር እያቀረበ መኾኑን ጠቅሷል። ሕገወጥ ግብይትን ለመቆጣጠርም እየሠራ መኾኑን አሳውቋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለኢንዱስትሪ መንደሮች ብቻ የሚያገለግል የኀይል አቅርቦት እንዲኖር እና ፋብሪካዎች ግብዓት በቀጥታ ከአምራቾች እንዲገበዩ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን አስረድቷል።
የተቀመጡ የመፍትሔ ሀሳቦች ፍሬ አፍርተው ወይዘሮ አሰለፈችን ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማኅበረሰብ የምግብ ዘይት ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲኾን ይፈልጋል፤ የጣፈጠ ምግብ በማዕዱ ላይ ይሻል።
ዘጋቢ: ደመወዝ የቆዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ግዳጁን እየተወጣ ነው” ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ
Next articleየልደት በዓልን በላሊበላ ለማክበር እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው።