በሀሰት መመስከር የሕግ ተጠያቂነቱ እስከምን ድረስ ይኾን?

4
ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) ሀሰት የሚለው ቃል ጥሬ ትረጉሙ ከዕውነት የራቀ ነገር ወይም ዕውነት የጎደለው ነገር ማለት ነው፡፡
ሀሰተኛ ነገሮችን ማስተባበል፣ ማግነን፣ መቅጠፍ እና ጉዳዩን መደበቅንም ይጨምራል። ሀሰት መናገር ወይም በሀሰት በሰው ላይ መመስከር ወይም በሀሰት ሰውን መወንጀል በሃይማኖት፣ በባሕል ይሁን በሞራል ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው።
ከዚህ ከፍ ሲልም የወንጀል ተጠያቂነትም እንደሚያስከትል የሕግ ምሁራን ይገልጻሉ። በዚህ ጹሑፍ በሀሰት መመስከር እና የሕግ ተጠያቂነቱ እስከምን ድረስ ይኾን? የሚለውን እንዳስሳለን። ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡን ደግሞ የአሚኮ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ ናቸው።
የአሚኮ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ በሀሰት መመስከር በግለሰቦች መብት እና ጥቅምም ኾነ በአጠቃላይ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል።
በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ በፍትሕ ሥራ ላይ ሊደረግ በሚገባው በዕውነተኛነት እና በታማኝነት ተግባር ላይ የሚፈጸም ወንጀል በሚለው ምዕራፍ በአንቀጽ 453 ስር በሀሰት መመስከር ማለትም ሀሰተኛ ትረጉም መስጠት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተደንግጓል።
ተጠያቂነትን በተመለከተም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 453 (1) መሠረት የዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ምስክር ኾኖ የቀረበ ማንኛውም ሰው ወይም ማንኛውንም ተከራካሪ ወገንን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት አስቦ ሀሰተኛ ምሥክርነት ወይም የልዩ አዋቂነት አስተያየት የሰጠ እንደኾነ ወይም ዕውነቱን የደበቀ እንደኾነ ያቀደው ሃሳብ ከግቡ ባይደርስ እና ግለሰቡን ባያስቀጣም እንኳ በቀላል አስራት እንደሚቀጣ ተቀምጧል ነው ያሉት።
ጉዳዩ ከባድ ከኾነም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ይኾናል።
በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ደግሞ ይህ ምስክር እውነቱን ለመናገር ምሎ ወይም ማረጋገጫ ሰጥቶ ማስቀጣት የሚፈልገውን አስቀጥቶ እንደኾነ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይኾናል።
ሀሰተኛ ምስክርነቱ የወንጀል ጉዳይ ቢኾንስ? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም ጉዳዩ የወንጀል ጉዳይ ከሆነ እና ተከሳሹ በመስካሪው ድርጊት ምክንያት የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተላለፈበት ወይም ከ10 ዓመት ጽኑ እስራት በላይ ተፈርዶበት እንደኾነ የተመሰከረበት ሰው በስህተት በተወሰነበት ቅጣት ልክ ሀሰተኛ መስካሪው ሊወሰንበት እንደሚችል በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ተቀምጧል ነው ያሉት የሕግ ባለሙያዋ።
ሕጉ ሀሰተኛ ምስክርነትን በወንጀልነት ከመደንገጉ በተጨማሪ በጽሑፍም ይሁን በቃል የሚደረግ የመተረጎም ወይም የማስተርጎም ተግባር የሚያከናውን ሰው ስለ ጉዳዩ ዕውነታውን እንዲያስቀምጥም አመላክቷል፡፡
በአንቀጽ(453) ንሑስ አንቀጽ 3 ላይ እንደሰፈረው ሀሰተኛ ትርጉም የሚሰጥ ማንኛውም ተርጓሚ ወይም አስተርጓሚ እንደ አግባቡ ለሀሰተኛ ምስክርነት ከላይ የተመለከቱት ቅጣቶች ተፈጻሚ ሊኾኑ ይችላሉ።
ሀሰተኛ ምስክርነቱ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ የማያደርስ ቢኾንስ ተጠያቂነት ያስከትል ይኾን?
የሕግ ባለሙያዋ ሀሰተኛ ምስክርነቱ ወይም ልዩ አስተያየቱ፣ በሀሰት በመተርጎሙ ወይም ማስተርጎሙ ተደርሶበት ፍርድ ቤት ወይም የዳኝነት ነክ ሥልጣን ያለው አካል በሚሰጠው ፍርድ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ የማይችል ቢኾን እንኳን ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ተጠያቂ እንደሚኾን ተደንግጓል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየአማራ ክልል የባሕል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና መስጫ እና የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
Next article“ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም እንዲረጋገጥ ግዳጁን እየተወጣ ነው” ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ