ምጣኔ ሀብታዊ ትግል እና ኮሮናቫይረስ

191

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2012 ዓ.ም (አብመድ) አቶ ዋሲሁን በላይ በግል የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ናቸው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ሊያስከትል ስለሚችላቸው ችግሮችና ከቀውሱ የመውጫ መንዶችን የሚያሳዩ ማብራሪያዎችን ለአብመድ ሰጥተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዋስይሁን በላይ የዓለም ኢኮኖሚን ኅልውና ለማዳን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዕጣ ፈንታችን እንዲወስን ሳይሆን የኢኮኖሚውን ተጋላጭነት በማያባብሱ ዘርፎች ላይ በመመሥረት መመከት እንደሚግ መክረዋል፡፡

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በታዳጊ ሀገራት የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያስከትልም ተንታኙ ተናግረዋል፡፡ በሰው ጉልበት ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያቸውን በአገልግሎት ዘርፉ ላይ አደራ የጣሉ ሀገራት በእንቅስቃሴ ገደቦቹ ሊሽመደመዱ እንደሚችሉ አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግብርና፣ ማዕድን እና ግንባታ ዘርፎች ላይ የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነትን በጥንቃቄ ለመከላከል የተሞከረ እየተሠራ እንደሆነ በመግለጽ ለጊዜው ዘርፎቹ ብዙም አለመጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ዋስይሁን “የኛ ሀገር ኢኮኖሚ ገዥ ኢኮኖሚ ነው፤ የውጭ ሀገር ጥሬ ዕቃዎችን የሚገዛ ጥገኛ ኢኮኖሚ ነው፤ የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚውን ኅልውና እንዲረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል” ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዓለም ገበያ ገዥ ባላጡት ቡና፣ አበባ፣ ስጋ እና ማዕድናት ላይ በትኩረት በመሥራት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

‘‘በኮሮናቫይረስ ወቅት የፋይናንስ ዘርፎቹ ግብይት እየቀነሰባቸው ነው፤ በቀላሉ የሚገበያቸው ስለሚያጡ ድጋፍ በማድረግ ኢኮኖሚው ላይ እንዲቆዩ ማድረግ ይገባል’’ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን መተካት የሚችሉ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማትን መደገፍ እንደሚገባም መክረዋል፡፡

‘‘ግብርናው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያረጋጋ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይቻላል’’ ያሉት አቶ ዋስይሁን ብዙ መሬቶች በሰብል እንዲሸፈኑ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ሽግግር እንደሚያደርግ ተስፋ ተደርጎ ሲሠራ ቢቆይም በአፈጻጸም ችግር ምክንያት ከግብርናው ቀጥሎ ከፍተኛ መሠረት የሆነው የአገልግሎት ዘርፉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ በሰላም እና ደኅንነትና በጤንነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ እንደኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መሰል ችግሮች በመጡ ቁጥር የቁልቁለት ጉዞው እንደሚፋጠን ነው ያለከቱት፡፡ በዚህ የተነሳም ‘‘ሠራተኞች ይቀንሳሉ፣ ለአገልግሎት ዘርፉ የሚካሄደው የገበያ ሰንሰለት ይቆረጣል’’ ነው ያሉት አቶ ዋሲሁን፡፡
እንደተንታኙ ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ትግል ጋር በመሆን በማዕድን ዘርፍ፣ በግብርና ዘርፍ፣ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች ብትሠማራ ኢኮኖሚዋን ከመዋዥቅ ልትታደግ ትችላለች፡፡

ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሚታመስበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ማግኘት እንድትችል ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች መጠናከር ማተኮርና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡
ሀገራት ምርት መቀበል ባለቆማቸው ጥንቃቄን በመጨመር የውጭ ምንዛሬ የሚሻው ገዥ ኢኮኖሚ እንዳይቀዛቀዝ ሊሠራ እንደሚገባም የኢኮኖሚ ተንታኙ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት መነሻ የግብርና ምርቶች በመሆናቸው ከዕቅድ በዘለለ አቅርቦትን የሚያሻሽል ከአመራረት እስከ ገበያ የሚደርስ ሰንሰለት መፍጠር እንደሚገባም መክረዋል፡፡

አቶ ዋስይይሁን በኮሮናቫይረስ ወረርሸኙ ሥራ አጥነት ወደምግብ እጥረት እንዳያመራ መሥራት እንደሚስፈልግም አስጠንቅቀዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት የነበረው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በገጠር ላይ የተመሠረተና የከተማውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ወደሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ለመፍጠር የተሄደበት ቢሆንም ገጠሩ ራሱን መግቦ ከተማውን መመገብ አለመቻሉን አመላክተዋል፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ ከተማ 25 በመቶ የአትክልትና ፍራፍሬ ፍጆታዋን በከተማ ግብርና ለመሸፈን የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በሌሎችም ከተሞች ማስፋት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

‘‘የከተማ ግብርና ላይ መሥራት የገበያውን ጫና እንዲቀንስ ያደርጋል’’ ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ ከኮሮናቫይረስ የኢኮኖሚ ጫና ለመውጣትም የውጭ ግንኙነቶችና ድጋፎች እንዲኖሩ መሥራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የረጂም ጊዜ ብድሮችን በማፈላለግ፣ በጀቶችን ለተመረጡ ፕሮጀክቶች በማዋል ከቀውሱ ለመውጣት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ለአብነት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ያሉ ኃይልን ለውጭ ገበያ (ኤክስፖርት ማድረግ) ማቅረብ የሚያስችሉ፣ በግብርና ዘርፍ ሰፊ ሥራ ዕድል ላላቸው እና ለመሠል የተመረጡ ፕሮጀክቶች በመመደብ ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና መመከት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ማኅበራዊ ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ እና የምግብ ባንኮች ሊኖሩ እንደሚገባም ተንታኙ አሳስበዋል፡፡

ከወረርሽኙ በኋላ ዕዳ ውስጥ ያልተዘፈቀ ኢኮኖሚ ሁኖ እንዲቆይና ከኮሮናቫረስ ማግሥት ኢኮኖሚው እንዲያንሠራራ የመዳረሻ ወይም የኢኮኖሚ ማግኛ ምንጮችን ማሻሻል፣ ማዘመን እና ዝግጁ የማድረግ ቅድመ ተግባራት ሊሠሩ እንደሚገባም አቶ ዋስይሁን ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ዘርፉ ኢትዮጵያ ካላት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች መዳረሻ አንጻር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል የሚችል ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፉ ተስፋ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ቱሪዝሙ ብቻ ሳይሆን ብዙ ማሻሻያ የተደረገበት የማዕድን ዘርፉ ሊሠራ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ እንደ አዲስ አበባው የለገሀር ኢንቨስትመንትና የአሊባባ የአይሲቲ ግብይት መጠናከር እንዳለባቸውና የካፒታል ገበያውን ወደግል ማዞር አስፈላጊ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ለመስኖ የተሰጠውን ትኩረት ማሳደግ፤ ኩታገጠም የአስተራረስን ልምድ ማዳበር፣ የግብዓት አቅርቦትና አጠቃቀሙን ማሳደግ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡

ሰሊጥ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ነጋዴዎች የሰሊጥ አመራረት ዘርፉን የሚያሳድግ የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቅመው ከመሥራት ይልቅ ግብርናውን እንዳለ ትቶ ወደ አገልግሎት ዘርፉ ሩጦ የመግባት ችግራውን መቅረፍ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራው ቢጠናከር ከአገልግሎት ዘርፉ ከሚገኘው ገቢ ይልቅ ግብርናው በርካታ የገበያ ትስስር ማዕከላትን ይፈጥራል፤ ገበያ የማረጋጋትና የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕድሉም አሁን ካለው ዕጥፍ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ተንታኙ ‘‘ገበሬው ትርፍ ምርት ባገኘ ቁጥር ‘ትራክተር እገዛለሁ’ ከማለት ይልቅ ከተማ ውስጥ ቤት መሥራትን የስኬት መዳረሻ አድርጎ የሚያየውን አካሄድ ለመቀየር ከአሁኑ መሥራት ይበጃል’’ ብለዋል፡፡

‘‘ኢትዮጵያ ግብርናውን ወደኢንዱስትሪ መር እለውጣለሁ የሚል እቅድ ስታወጣ የገበሬ ልጆችን በማስተማር አዘምናለሁ የሚለው አስተሳሰብ ነበራት’’ ያሉት አቶ ዋስይሁን ይህ እንዲተገበር በመንግሥት ተቋማት ተቀጥሮ የመኖር አስተሳሰብን መቀየር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የኢትጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የግብርና ምርቶችን ወደአግሮ ኢንዱስትሪ መቀየር የትውልዱ አዲሱ የሥራ ዘርፍ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleለሕዳሴ ግድብ አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ኬንያ ገለጸች።
Next articleመንግሥት የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የገባውን ቃል እንዲፈጸሙላቸው የበየዳ ወረዳ ነዋሪዎች ጠየቁ።