
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን በቅርቡ በኮሚሽንነት መቋቋሙን አስመልክቶ እና እያከናወናቸው በሚገኙ ወቅታዊ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ እንዳሉት ሚሊሻ በሰላም ወቅት የልማት አርበኛ፣ ሀገር ችግር በገጠማት ጊዜ ደግሞ ወታደር ኾኖ ሕግ እና ሥርዓትን የሚያስከብር ነው።
“ሰላም የራቀው ሕዝብ በሙሉ አቅሙ አያለማም፣ ወጥቶ ለመግባትም ይቸገራል” ያሉት ኮሚሽነሩ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የተሰጠውን ተልዕኮ በተሻለ መልኩ በማከናወን የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ በአዋጅ ወደ ሚሊሻ ኮሚሽንነት መሻሻሉን ገልጸዋል።
የማሻሻያ አዋጁ የአማራ ክልል ያዘጋጀውን የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ ለማሳካትም ያለመ መኾኑን ጠቅሰዋል። ተቋሙ የሕዝብ አገልግሎት ተደራሽነትን ያረጋገጠ እንዲኾን ለማስቻልም ነው አዋጁ ላይ ማሻሻያ ያደረገው ብለዋል።
ለፌዴራሉም ኾነ ለክልሉ ሕገ መንግሥት እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ታማኝ እና ተገዥ እንዲኾን፣ ተልዕኮውን በብቃት የሚፈጽም፣ የሚመራ ሚሊሻ እና የሰላም አስከባሪ ኀይል ማደራጀት ተገቢ ኾኖ በመገኘቱ የማሻሻያ አዋጁ ወጥቷል ነው ያሉት።
ሚሊሻን ከሌሎች የጸጥታ አካላት ልዩ የሚያደርገው ከሕዝብ ተመልምሎ እስከመንደር ድረስ የተዘረጋ መኾኑ እና ከሕዝብ ጋር እየኖረ ነጻ ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠቱ ነው ብለዋል። የማሻሻያ አዋጁ መዘጋጀቱ የኮሚሽኑን መሪዎች እና ባለሙያዎች የጡረታ ዕድሜ፣ የሰላም አስከባሪዎችን እና የሚሊሻ አባላትን ደግሞ የአገልግሎት ዘመን፣ ጥቅማጥቅሞች እና ማበረታቻዎች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በአዋጅ ተደግፎ የተደረገው ለውጥ በተዋረድ ያለውን የክልሉን የጸጥታ ኀይል ይበልጥ በማጠናከር እና ወደ ሥራ በማስገባት የሕዝብን ሰላም እና ልማት ለመጠበቅ የሚያስችል የሪፎርም አካል መኾኑንም ጠቁመዋል።
የተቋሙ ስያሜም በክልል ደረጃ ሚሊሻ ኮሚሽን፣ በዞን ደረጃ ሚሊሻ መምሪያ፣ በወረዳ ደረጃ ደግሞ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ተብሎ እንደሚጠራ አስታውቀዋል።
“ሚሊሻ ሁለገብ የሰላም እና የልማት አርበኛ ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ ሕዝቡ ሰላሙን ከሚጠብቁለት የሚሊሻ አባላት ጎን በመቆም ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ባለፉት ጊዜያት ጫካ በመግባት የአማራ ክልልን ሕዝብ ሲበድሉ የቆዩ አካላት አሁን ላይ ተጸጽተው ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሰላም እየተመለሱ መኾናቸውን አንስተዋል። በበደላቸው ተጸጽተው ሕዝብን በልማት ለመካስ የመጡትን በሙሉ እንዳመሠገኑም ገልጸዋል።
አሁንም ድረስ ጫካ ለጫካ እየተሹለከለኩ በጥፋት መንገድ የቀጠሉ አሉ፤ እነዚህን አካላት በቃችሁ፣ ሕዝባችሁ አዝኖባችኋልና ወደ ሰላም ተመለሱ ማለት እፈልጋለሁ” ነው ያሉት።
የሰላም ጥሪን ተቀብለው ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩም ጠይቀዋል። መንግሥት የምትፈልጉትን ጥያቄ በሰላም አቅርቡ ብሏል፤ በፈለጉት ቦታ እና ሁኔታም ለመወያየት በሩ ክፍት ነው፤ በተግባርም አሳይቷል፤ አሁን የሚጠበቀው የታጣቂዎች ምላሽ ብቻ ነው ብለዋል። የመንግሥትን ትዕግስት እና የሰላም ጥሪ ወደጎን በመተው ሕዝብን እየበደሉ ለመቀጠል በሚፈልጉት ሕገወጦች ላይ ግን ሕግ እና ሥርዓት የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ሰላሙን ከሚጠብቁለት የጸጥታ ተቋማት ጋር መቆም እና መተባበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ የወጡ ሚሊሻዎችን ቤተሰቦች መንከባከብ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባዋልም ነው ያሉት።
ክልሉን የሚያወድሙ እና የሕዝብን ሰላም የሚያውኩትን ግን በግልጽ አውግዞ በቃ፣ ልቀቁን፣ ልማታችንን አታስተጓጉሉብን ማለት እንደሚገባም አመላክተዋል። በማወቅም ኾነ ባለማወቅ፣ በውዴታም ኾነ በግዴታ ለሕገ ወጦች ስንቅ እና ሌሎች አቅርቦቶችን የሚያደርሱ አካላትም “ነገ የሚነክሳቸውን ዛሬ እያጎረሱ” መኾኑን መርምረው በመገንዘብ ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ይልቁንም ወደ ሰላም እንዲመጡ መጠየቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ወቅቱ የተለያዩ በዓላት የሚከበሩበት መኾኑን ተከትሎ የሚሊሻ አባላት ተገቢውን የሰላም ማስጠበቅ ዝግጅት ማድረጋቸውንም በመግለጫቸው አንስተዋል። እንግዶች በሰላም እንዲዘዋወሩ እና የክልሉ ቱሪዝም እንዲነቃቃ ሰላም ያስፈልጋል፤ በየቦታው ያሉ የሚሊሻ አባላትም ከሕዝቡ ጋር በመኾን የእንግዶች ቆይታ ያማረ እንዲኾን የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
