የእስቴ – ስማዳ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በታኅሣሥ 2018ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው።

5
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በደቡብ ጎንደር ዞን ከእስቴ – ስማዳ የሚሠራው የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡
‎መንገዱን ለማሳለጥ የተቋቋመው የሀገር ሽማግሌዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ መምህር ተስፋዬ አካሉ የመንገድ ሥራው ከተጀመረ መቆየቱን ተናግረዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም ኮሚቴ ተቋቁሞ እያስተባበረ እና ለመንገድ ሥራው የሚያደናቅፉ ችግሮችን በምክክር እየፈታ እንዲሠራ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
‎አሁን ላይ በከተዎች ውስጥ ውስን የማጠናቀቅ ሥራዎች ብቻ እንደቀሩ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን ነው ያሉት።
‎‎ለመንገዱ መሠራት የአካባቢው ማኅበረሰብ አስፈላጊውን ትብብር ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡የመንገዱ መሠራት ወደ ዞኑ እና ወደ ባሕር ዳር ከተማ ለመሄድ የነበረውን እንግልት ቀንሶልናል፤ ምርትን ወደ ከተማ ወስዶ ለመሸጥ እና በአጭር ጊዜ መድረስ አስችሎናል ነው ያሉት፡፡
‎የወገዳ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አስናቀው ቆዬሁ መንገዱን በሦስት ዓመታት ገንብቶ ለማጠናቀቅ ቢታቀድም በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ በመቆየቱ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡ የነበረውን ችግር ከማኅበረሰቡ ጋር በመፍታት ሥራው ተጀምሮ አሁን ላይ የ700 ሜትር ሥራ ብቻ እንደቀረ ገልጸዋል፡፡
‎በተቋራጩ በኩል ለአርሶ አደሮች የመሬት ጉዳት ካሳ ክፍያ አለመከፈል እና በመንግሥት በኩል ደግሞ ለአርሶ አደሮች ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ አለመከፈሉን በችግር አንስተዋል፡፡
‎የመንገድ ሥራው መጠናቀቅ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እና ለተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ያጠናክራል ብለዋል፡፡ አካባቢው ምርታማ በመኾኑ ምርቱን ወደ ሌላ አካባቢ ወስዶ ለመሸጥ እና የፋብሪካ ምርቶችን ወደ ከተማው ለማምጣት ምቹ ኹኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።
‎የእስቴ ስማዳ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ ፍርዬ መንግሥቴ ሥራው በ2011 ዓ.ም መጀመሩን እና 54 ነጥብ 42 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
በ2016 ዓ.ም 49 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር አስፋልት ተነጥፎ ለማጠናቀቅ ተቃርቦ እንደነበር ያነሱት ሥራ አሥኪያጁ በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ንብረት በመዘረፉ ሥራው ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
‎አሁን ላይ መንገዱ 98 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል፤ የቀሪ 700 ሜትር መንገድን የማጠናቀቅ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡ አስፋልት ለማንጠፍ አንድ ሙሌት ብቻ እንደቀረ አንስተዋል። እስከ ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
‎ማኅበረሰቡም ለመንገድ ሥራው አስፈላጊውን ትብብር አድርጓል ብለዋል፡፡ መንግሥት ባልከፈላቸው የካሳ ክፍያዎች ምክንያት ሥራውን በማከናወን ረገድ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
‎በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር ፕሮጀክት አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ መንገዱን በታኅሣሥ 2018ዓ.ም ለመጨረስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
‎ለፕሮጀክቱ መዘግየት የዲዛይን ለውጥ እና የጸጥታ ችግሮች ምክንያት እንደነበሩም አንስተዋል። ችግሩ የተፈጠረው ለመጨረስ 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ሲቀር እንደነበረ ነው የገለጹት፡፡ ያም ኾኖ በብዙ ርብርብ ሥራው እንዲቀጥል ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
‎የአርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ ይከፈል የነበረው ችግር ተፈትቶ በመንገዶች አሥተዳደር በኩል ክፍያው እንዲፈጸም መወሰኑን እና በሂደት እንደሚከፈልም ገልጸዋል፡፡
‎‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ተግባራት እንደሚከናወን ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
Next article“በክልሉ የሚገኙ ፕሮጀክቶች የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ ሚናቸው ከፍ ያለ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)